የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በሶማሌ ክልል ውስጥ ለሚገኙ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስረከበ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ዜጎች በዕዉቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫን እንዲያደርጉ እና የዜግነት መብት እና ኃላፊነታቸውን በመገንዘብ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስችል ዘንድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም መሠረት የሥራ ክፍሉ በቦርዱ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ስድስት ከተሞች ማለትም፤ ጅግጅጋ፣ ቀብሪበያህ፣ አራርሶ፣ ደጋህቡር፣ ቀብሪደሀር፣ እና ጎዴ ውስጥ ለሚገኙ 10 የሁለተኛ ደረጃ እና አምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለጅግጅጋ እና ቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲዎች በአማርኛ እና በሶማልኛ ቋንቋዎች እንዲሁም በብሬል የተዘጋጁ አምስት የተለያየ ይዘት ያላቸው ማለትም፤ ‘የምርጫ ሒደት’፣ ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ ‘ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች፤‘ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ እና ‘ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት’ በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ በቁጥር 17,716 ብሮሸሮች እና መጽሔቶችን አስረክቧል፡፡
የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ለዜጎች ተደራሽ ማድረጉ አካታች ለሆነ ምርጫ እና ዴሞክራያዊ ተሳትፎ የሚኖረው አስተዋፆ ጉልህ በመሆኑ ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየሠራበት ይገኛል፡፡

