የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በምርጫ ሂደት ዙሪያ የተዘጋጁ የህትመት ውጤቶችን በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር አሰራጨ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ከሚያርግባቸው ስልቶች መካከል የተለያዩ መረጃዎችን እና ትምህርቶችን ያያዙ የህትመት ውጤቶች ስርጭት አንደኛዉ መንገድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በቦርዱ የድሬደዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በድሬደዋ አስተዳደር ውስጥ ለሚገኙ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ፣ የድሬደዋ አስተዳደር የሕዝብ ቤተ-መጻህፍት እና በከተማ እና በገጠር ለሚገኙ 28 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ ፤ እና በሶማልኛ ቋንቋዎች እንዲሁም በብሬል የተዘጋጁ አምስት የተለያዩ ይዘት ያላቸው ማለትም፤ ‘የምርጫ ሒደት’፣ ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ ‘ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች’ ፣’ ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ እና ‘ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት’ በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ በቁጥር 3530 ብሮሸሮች እና መጽሔቶችን አስረክቧል፡፡
ቦርዱ እነዚህን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና የምርጫ ሒደት ይዘቶችን የያዙ የህትመት ውጤቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ በክልሎች እና በከተማ አስረዳደሮች ስር ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የሕዝብ ቤተ መጻህፍት ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉ ዜጎች በምርጫ ሒደት ውስጥ የሚኖራቸውን መብት እና ግዴታዎች እንዲያውቁ ከማስቻሉም በላይ አካታች ለሆነ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እና በተለይም የመጀመሪያ ጊዜ መራጮችን ተሳትፎ በማጉላት ረገድ ሁነኛ አስተዋፆ የሚኖረው በመሆኑ የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በዚህ ረገድ በስፋት እየሠራበት ይገኛል፡፡



