የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በአፋር ክልል ውስጥ ለሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሰራጨ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለምርጫ ሒደት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዜጎች በቂ ግንዛቤን ያገኙ ዘንድ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ መልዕክቶችን ተደራሽ ማድረግ ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በቦርዱ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በአፋር ክልል ውስጥ ለሚገኙ የሰመራ፣ ሎግያ፣ አይሳ፣ ዱብቲ እና ሚሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም አሳይታ መምህራን እና ሰመራ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች በአማርኛ እና በአፋርኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አምስት የተለያዩ ይዘት ያላቸው ማለትም፤ የምርጫ ሒደት፣ ምርጫ በኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች፣ ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ፣ እና ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ በቁጥር 11900 ብሮሸሮች እና መጽሔቶችን አስረክቧል፡፡
ቦርዱ እያከናወናቸው ከሚገኙ ሥራዎች መካከል በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ የዜጎችን ተሳትፎ ለማጉላት እና በዕዉቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የተለያዩ መረጃዎችን እና ትምህርቶችን የያዙ የህትመት ውጤቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ ተደራሽ ማድረጉ አካታች ለሆነ የዴሞክራሲ ተሳትፎ ጉልህ አስተዋፆ የሚኖረው በመሆኑ ለወደፊትም ይህን መሰል ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡



