ቦርዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ተሳትፎ እንዲጎለብት እየሠራ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁሉም የሀገራችን ዜጎች የፓለቲካ ተሳትፎ መብታቸው በተለይም የመመረጥና መምረጥ መብታቸው እንዲጎለብት አካታች የምርጫ ሥርዓትን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ይህንንም ዕውን ለማድረግ ቦርዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫ ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያላቸውን ፍላጎት እና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በዳሰሳ ጥናት በመለየት ምቹ የምርጫ ከባቢ ለመፍጠር ኢስት አፍሪካ ከተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአማካሪ ድርጅትነት ቀጥሮ በማስጠናት ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለታቀደው የዳሰሳ ጥናት አማካሪ ድርጅቱ የጥናቱን መነሻ ዕቅድ ሪፖርት ለቦርዱ ሥራ አመራር፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ዕቅዱን (Inception plan) የሚያጎለብቱ የሀሳብ ግብዓቶችን (ምክረ ሃሳቦችን) ሰብስቧል።
አንድን ምርጫ ሁሉን አቀፍና ፍትሐዊ ከሚያሰኘው መስፈርቶች አንዱ በአካታችነት ማዕቀፍ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በምርጫ ሂደት በመራጭነትም ሆነ የመመረጥ መብት እንዳላቸው ለማስረፅ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ጥናቱ በኢትዮጵያ አካታች የምርጫ ሥርዓትን ለመገንባትና ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።
ጥናቱ በመሠረታዊነት ከሚዳስሳቸው ጉዳዮች መካከል አሁን በሥራ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማቅፎች፣ ፓሊሲዎች እና አሠራሮቾ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚገባ ከማስተናገድ አኳያ ያላቸውን አግባብነት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ያላቸው እና ሊኖራቸው ስለሚገባ የተሳትፎ ደረጃ፣ ተፈናቃዮቹ በምርጫ ሂደቱ እንዲሳተፉ እንዲሞላላቸው የሚፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አደረጃጀት ለተፈናቃዮች ምቹ መሆኑ፣ የባለድርሻ አካላት ሚናና ግዴታዎች ምን መሆን አለባቸው የሚሉ ሃሳቦችን መፈተሽ ይገኙበታል።
ወ/ሮ ሜላትወርቅ ይህን ሥራ በማስተባበር ውጤታማ እንዲሆን በመትጋት ላይ የሚገኙትን የቦርዱን ሥርዓተ ጾታና ማህበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል ባለሙያዎችን፣ በአውደ ጥናቱ ግብዓት ለሰጡ እና መነሻ ዕቅድ ሪፖርቱ እንዲሻሻል አስተዎፅኦ ላበረከቱ የቦርዱ ሥራ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከመልከዓ ምድር አኳያ የዳሰሳ ጥናቱ የተወሰኑ ክልሎችን ማካተቱ ታውቋል። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫ ሂደት መሳተፍ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ቀያቸው በመመለስ ወይም ተፈናቅለው ከሚገኙበት አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲገነቡ እና እንዲቀላቀሉ በማድረግ እና ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ ሂደት ላይ ጠቃሚ አስተዋፅኦ እንዳለው የዳሠሠ ጥናቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።

















