Skip to main content

የምርጫ ጣቢያዎችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ የመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) ለማካለል ቦርዱ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገራችን የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ ሥርዓት በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) ታግዞ ለማዘመን እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በመጀመሪያ ዙር የምርጫ ጣቢያዎችን በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) ለማካለል የታቀደው ሥራ በድሬደዋ ሁለት፣ በሐረሪ ሶስት፣ በሲዳማ አስራ ዘጠኝ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ሰባት የምርጫ ክልሎች ላይ እንደሚተገበር ታውቋል።

ይህንንም ተከትሎ በምክክር መድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ፤የሐረር እና የሲዳማ ክልሎች እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የክልል አስተዳደር አካላት፤ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፤ የፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የየክልሎቹ የምርጫ ላይዘን ኦፊሰሮች ታዳሚ ነበሩ::

የምርጫ ጣቢያዎችን በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት የማደራጀት ፋይዳ በዋነኛነት የምርጫ ጣቢያዎቹን መረጃ ወቅታዊ ለማድረግ፣ የምርጫ ጣቢያዎቹን ትክክለኛ መገኛ ለማወቅ፣ ጣቢያዎቹ በምርጫ ሕጉ መሠረት በተፈቀደው ቦታ ስለመቋቋማቸው ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና ለታዛቢዎች ምርጫ ጣቢያዎችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግና የምርጫ ቁሳቁሶችንም በቀላሉ ለማሠራጨት እና ምቹ የምርጫ ጣቢያዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመራጮች ለማመቻቸት ያለመ ነው።

በአራቱ ክልሎች ለመጀመሪያ ዙር የምንሰራው ሥራ ሞዴል ሆኖ በተቀሩት ሌሎች የሀገራችን ክልሎች ለመተግበር መደላድል ይፈጥራል ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በክልሎቹ የምትሰጡን የምርጫ ጣቢያዎች ቢያንስ 7ኛውን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እንዲያስችለን በቀላሉ የማይቀየሩ ወይም ለሌላ የልማት ሥራዎች የማይለወጡ እና ቦታዎቹም በቂ የምርጫ ቁሳቁስ ማስቀመጫ ስቶር እንዲኖራቸው እንድታደርጉ ከወዲሁ ትብብራችሁን እንጠይቃለን ብለዋል።

የመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) ለመራጮች አመቺ ከመሆኑም ባሻገር የምርጫ ኦፕሬሽን እና የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት ወጪ ቆጣቢ እና ቀልጣፋ እንዲሆኑ ያስችለናል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ የምርጫ ጣቢያዎች መጠሪያዎች ለመራጩ በቀላሉ የሚያዙና ደረጃቸውን የጠበቁ ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።

ከአራቱም ክልሎቹ የመጡ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀደውን ሥራ አድንቀው፣ ከክልሎቹ የመንግስት አስተዳደር አካላት የሚጠበቀውን ድጋፍ እና ትብብር በቁርጠኝነት እንደሚተገብሩ ቃል ገብተዋል።

የምርጫ ጣቢያዎቹን በቴክኖሎጂ በተደገፈ ሥርዓት በማካለል ጣቢያዎቹ የሚገኙበትን ገለልተኛ እና ትክክለኛ ቦታ የመለየት፣ የመመዝገብ እና ምርጫ ጣቢያዎቹን በቋሚነት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ለማድረግ በሀገራችን የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) የማካለል ሥራው በሶስት ዙር እንደሚከናወን ታውቋል።

Share this post