የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የመረጃ ኃብቶች ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ተቋማዊ ትውስታዎችን በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍን ዓላማ ያደረገ ሥልጠና ከቦርዱ የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች እየሰጠ ነው፡፡
ዘመናዊ የመረጃ አስተዳደርና የመረጃ ኃብቶች ጥበቃና እንክብካቤን በተመለከተ ከየካቲት 3 - 14 ቀን 2017ዓ.ም. በሚሰጠው ሥልጠና ሠልጣኞች ከምርጫ ጋር የተያያዙ የመረጃ ኃብቶች እንዴት እንደሚሰበሰቡ፣ እንደሚደራጁ እና እንደሚጠበቁ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላል ተብሏል፡፡
በሥልጠናው መክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የታሪክ ጥበቃ ክፍላችን የበርካታ ሠነዶች እና መዛግብት ባለቤት በመሆኑ ለአጥኚዎች እና ተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር ዕምቅ አቅም ያለው እና ሀገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ያሉንን መረጃዎች እና መዛግብት በአግባቡ አደራጅተን መጠበቅ ይገባናል ብለዋል፡፡
ለአስር ቀናት በሚቆየው ሥልጣና ሠልጣኞች በትጋት ሠልጥነው የሚጠበቅባቸውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ አደራ ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሥልጠናውን ለሚሰጠው የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡




