Skip to main content

የቦርዱን የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማስተባበሪያ ቢሮ የማቋቋም ፋይዳ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 23 እና 24 መሠረት ቦርዱ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ምርጫ የሚያስተባብሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንደሚያቋቁም ይደነግጋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልተማከለ የምርጫ አስተዳዳር ሥርዓቱ (Decentralized electoral administration) በምርጫ ዑደት ውስጥ ከቅድመ ምርጫ አንሥቶ እስከ ድኅረ ምርጫ ሒደቶች ድረስ ያሉትን ክንዋኔዎች ለህዝብ ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳው ዘንድ በቦርዱ ዋና መ/ቤት የሚገኝ ራሱን ችሎ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን የሚያስተባብር የሥራ ክፍል አቋቁሟል፡፡

የክልል ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ የሥራ ክፍሉ ከሚያናከውናቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል በክልል የተቋቋሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን እና አዲስ በመደራጀት ላይ ያሉ ተጨማሪ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በመዋቅር፣ በሰው ኃይል፣ በአሠራር ስርዓት እና በቴክኖሎጂ እንዲጠናከሩ ማድረግን ያካትታል፡፡

ቀደም ሲል ቦርዱ በሀገር አቀፍ ደረጃ አስራ ሁለት (12) ብቻ የነበሩትን የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የክልሎችን የቆዳ ስፋት፤ የህዝቡን አሰፋፈር እና የመራጮችን ቁጥር ማዕከል በማድረግ ጽ/ቤቶቹን ወደ ሀያ ሁለት (22) አሳድጓል፡፡

በዚህ መሠረት ቀድም ሲል በኦሮሚያ አንድ፣ በአማራ አንድ፣ በትግራይ አንድ፣ በሶማሌ አንድ፣ በአፋር አንድ፣ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ አንድ፣ በጋምቤላ አንድ፣ በሐረሪ አንድ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ አንድ፤ በአዲስ አበባ አንድ፤ በድሬዳዋ አንድ፣ በሲዳማ አንድ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አንድ፣ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ከነበሩት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በተጨማሪ በኦሮሚያ አራት፤ በአማራ ሶስት እና በሶማሌ አንድ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ለማቋቋም ወስኖ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ቦርዱ በድምሩ ሀያ ሁለት (22) የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲኖሩት ያስችለዋል፡፡

ባልተማከለ የምርጫ አስተዳዳር ስርዓት አወቃቀር የምርጫ አስፈጻሚ አካል ተግባራት ቀጣይነት ያላቸው እና በምርጫ ወቅት የሚከናወኑ ሥራዎችን ለህዝብ ተደራሽ ባደረገ አግባብ በሚከናወንበት ጊዜ ምርጫው በአካታችነት፣ በግልፀኝነት፣ ጥራት ባለው የአገልግሎት ዘዬ ስለሚሰጥ፣ ቅቡልነት እና ተዓማኒነት ያለው አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ መደላድል ይፈጥራል፡፡

Share this post