የቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አተገባበር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፉ አድርጎ ያስጀመረውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ስልታዊ ግቦች እና ዓላማዎች እንዲሳኩ በየደረጃው ያሉ የቦርዱ ሠራተኞችን ስለስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ይዘት እና አተገባበር ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተካሄዱ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂያዊ እቅድ ስኬታማነቱ የሚረጋገጠው እያንዳንዳችን የቦርዱ ሠራተኞች እና ኃላፊዎች በምናበረክተው ጉልህ አስተዋፅኦ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለስትራቴጂያዊ ዕቅዱ እውን መሆን አሁን እያሳያችሁት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ይጠበቃል ብለዋል።
ከ2016/17 ዓ.ም. እስከ -2020/21 ዓ.ም እየተተገበረ ያለው ስትራቴጂክ ዕቅድ ስድስት አምዶችን (pillars) ማለትም የምርጫ ሕግ ማዕቀፍ፣ የዜጎች ተሳትፎና የግብ ትስስር፣ የምርጫ ሥራዎች፣ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና አጋርነት፣ ተቋማዊ ለውጥና ግንባታ እንዲሁም የምርጫ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀ ሰነድ ነው።
የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ የአካባቢ ምርጫና ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት መሰረት እንደሆነ ታውቋል።