የ6ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንዲሳካ የማስተባባር እና የክትትል ሥራ ያከናወኑ የክትትል ቡድኖች የሥራ ሪፓርት ተገመገመ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰኔ13 ቀን 2013 ዓ.ም. እና መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. 6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ በማይቻልባቸው ምክንያቶች ምርጫ ሳያካሂዱ በቀሩት በቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ አፋር፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልሎች የተካሄዱ የቀሪና ድጋሚ ምርጫዎች እንዳይስተጓጓሉ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተዋቅረው፤ ስምሪት ተሰጥቷቸው የነበሩ 27 የክትትል ቡድኖችን የሥራ አፈፃፀም ሪፓርት የተገመገመበት መድረክ አካሄደ።
በመርሃ ግብሩ የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የክትትል (Monitoring) ቡድን አደራጅተን ማሰማራት ከጀመርን ጊዜ አንስቶ የቦርዱ ምርጫ የማስፈፀም ዋነኛ ተልዕኳችን አይነተኛ መሻሻል አምጥቷል፤ በሂደቱም አሠራሮቻችንን ዳግም ለመፈተሽ በርካታ ትምህርቶችን መቅሰም ችለናል ብለዋል።
በጫካ፣ በበረሃ፣ በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልካዓ ምድር ሁኔታ ምንም ሳይበግራችሁ የቀሪና ድጋሚ ምርጫዎች እንዲሳኩ ስላደረጋችሁ ቦርዱም፣ ሀገራችሁም ታመሰግናችኋለች ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ በዚህ ልምድ በተለዋወጥንበት መድረክ የሰማናቸውን ችግሮች በሕግ፣ በሥርዓት እና በቴክኖሎጂ በመፍታት የተሻለ የምርጫ አፈፃፀም ስርዓት ተግባራዊ እንደርጋለን ብለዋል።
በመርሀ- ግብሩ በቦርዱ የኦፕሬሽን የሥራ ክፍል በምርጫ ዑደቶች (በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ) በምን ጉዳዮች ላይ ነው ክትትል ማድረግና የእርምት እርምጃ መወሰድ ያለበት?፣ የክትትል ሥራዎች እንዴት ይሠራሉ?፣ የቦርዱን የምርጫ ማስተባበር እና ክትትል ሥርዓት እንዴት እናዘምነው? እና በምርጫ ሂደት የክትትል አስተዳደር ሥርዓት ደረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ ምን ይደረግ?፣በሚሉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም በቦርዱ የስርዓተ- ጾታና ማህበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል አማካይነት የክትትል ቡድኖቹ የክትትል ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ በምርጫ ሂደት የሥርዓተ- ጾታና ማህበራዊ አካታችነት ዝርዝር ጉዳዮችን እንዴት መታቀድ እና መተግበር እንዳለባቸው ሥልጠና ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩም መጨረሻ በ6ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንዲሳካ የማስተባባር እና የክትትል ሥራ ላከናወኑ የቦርዱ ሠራተኞች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።