Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ላይ ስለነበረው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በታቀደው የዳሰሳ ጥናት መነሻ እቅድ ላይ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ላይ ስለነበረው የአካል ጉዳተኞች ውክልና እና ትርጉም ያለው ተሳትፎን በተመለከተ በምርጫ ቦርድ ለታቀደው የዳሰሳ ጥናት በቀረበ መነሻ እቅድ (Inception Plan) ላይ የምክክር መድረክ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. አካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የዳሰሳ ጥናቱን እንዲሠሩ በቦርዱ ለተቀጠሩ አማካሪ ቡድኖች ጥናቱን ለማዳበር ግብዓት የሚሆን መረጃዎችን መሰብሰብ እና ባለድርሻ እና አጋር አካላት በጥናቱ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ከፍ ማድረግ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት፤ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከጋራ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት፤ ከህብረት ለምርጫ፤ ከቦርዱ የተለያዩ ሥራ ክፍል የተውጣጡ ሠራተኞች እና ከጥናቱ አማካሪ ቡድን /Study Advisory Groups/ የተወከሉ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ባለድርሻ እና አጋር አካላት በዳሰሳ ጥናቱ ላይ የታዩ ክፍተቶችን፤ያልተስተዋሉ ጉዳዮችን እና ሊካተቱ የሚገባቸውን ሀሳቦች አንስተው ሰፊ ውይት ከተካሄደ በኃላ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Share this post