Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ህጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ

ኢህአዴግ በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሃት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል። የግንባርን መፍረስ የመወሰን ሥልጣን የቦርዱ በመሆኑ ግንባሩም ሆነ ህወሃት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቀመንበራት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎ መሠረት በማድረግ ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። በመሆኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመስረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል። በመሆኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የግንባሩ መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል። በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስት ማለትም አዴፓ ኦዴፓ እና ደኢህዴን ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መመስረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በህጉ መሠረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።

  1. ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረትና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
  2. በኢህአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
  3. ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት 3/4ተኛው ለብልጽግና ፓርቲ (የሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ¼ተኛ ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
  4. ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በህጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል (ውሳኔው በጽሁፍ የሚደርሳቸው ይሆናል)።

Share this post