ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ


ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በተለያዩ የመንግስትና የግል ዘርፎች ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ ሲሆን በተለያዩ የአመራር ስፍራዎችም ላይ ሠርተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ድርጅቱን ለሁለት ዓመታት በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ያገለገሉ ሲሆን በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫም ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

ወ/ሮ ሜላትወርቅ የህዝብ ተቋማትን /public sectors/ ከመቀላቀላቸው በፊት ከ12 ዓመታት በላይ የሕግ ቢሮ በመምራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን እና በተለያዩ ዘርፎች ያሉ የቢዝነስ ተቋማትን በሕግ አማካሪነትና ሕግን የተመለከቱ ሙያዊ ድጋፎችን በመስጠት አገልግለዋል።

በመጀመሪያዎቹ ሥራ የጀመሩባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃዎች በሕግ ማስከበር መምሪያ፣ በኦፕሬሽንስ መምሪያ እና በፍትሐብሔር ጉዳዩች ሥራ ክፍል በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡

ወይዘሮ ሜላትወርቅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ/ Law / የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሰላምና ደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ደግሞ በሰላምና ደህንነት /Peace and Security/ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር /Public Administration/ ሁለተኛ ዲግሪ ተቀብለዋል።