የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ ከአስተዳደር እና ጸጥታ አካላት ጋር ምክክር አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙት የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች የሚያካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ከአስተዳደር እና ጸጥታ አካለት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ የሕዝብ ውሣኔው አጠቃላይ ዕቅድና አፈጻጸሙን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል። የህዝበ ውሳኔውን ሰላማዊነት ከማረጋጋጥ እና ከሎጅስቲክስ አንፃር የክልሉ እና የአካባቢ አስተዳደር መዋቅሮች ያለባቸው ሀላፊነት በተመለከተም ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከእነዚህ መካከል የምርጫ ጣቢያዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የቦርዱ ሰራተኞች ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል፡፡ በምርጫ ፀጥታ ዕቅድ አወጣጥ ላይ በሲዳማ ሕዝበ ውሣኔ አፈፃፀም ላይ የተወሰዱ ልምዶችን በተመለከተ በወቅቱ የሲዳማ ም/ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት የተወካዮች ም/ቤት አባል አቶ ሰሎሞን ላሌ ዝርዝር ገለፃ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።
በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ስለ ማዕከላት አወቃቀር፣ ስለ ጊዜ ሰሌዳው ርዝማኔ እና ስለአስፈፃሚዎች ምልመላ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በነጥቦቹ ላይ በሰጡት ምላሽ ከዚህ በፊት ከነበሩት አስፈጻሚዎች መሀከል ምልመላ እንደሚደረግ ገልፀው ምርጫ ራሱን የቻለ ክህሎት የሚጠይቅ ስለሆነ ልምድ ያላቸውን መቅጠር የተሻለ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ሆኖም በሂደቱ የስነ ምግባር ጉድለት ያሳዩት እንደማይሳተፉ በመድረኩ ተገልጧል፡፡
በሌላ በኩል የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልልን አስመልክቶ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው የጸጥታ ሁኔታ ዝርዝር ዕቅድ አውጥተን እየሰራን ነው ሲሉ የክልሉን ዝግጁነት ገልፀዋል። የምክክር መድረኩን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የመድረኩን ተሳታፊዎች በማመስገን የፀጥታም ሆነ የሎጂስቲክስ ሥራዎችን በአፋጣኝ መከናወን እንደሚኖርባቸው በአፅንኦት አስገንዝበዋል። በእለቱ በአርባ ምንጭ ከተማ የተቋቋመው የህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሁሉም የምክክሩ ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል።