የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልል ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሕግ ማዕቀፍ ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ ማዕቀፍ ላይ በማተኮር ለቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሥልጠና የሰጠው ነሐሴ 10 እና 11 ቀን 2014 ዓ.ም ነው።
ሥልጠናው በቦርዱ አመራር አባል የሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት ንግግር ተከፍቷል። አመራሩ በንግግራቸው የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች በ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የነበራቸውን አስተዋፅዖ በማንሳት ምሥጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም ቦርዱ እንደ አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ በጊዜው በርካታ እቅዶች ቢኖሩም ከጊዜና ከሁኔታዎች አንጻር የታቀደውን ሁሉ በሚፈለገው መጠን መፈፀም እንዳልተቻለ የጠቆሙ ሲሆን፣ አሁን ግን እነዚህን ጉዳዮች ለመተግበር አመቺ ሁኔታ ስለተፈጠረ በተለይ በቀጣይ ለሚደረገው ትልቅ ዐቅም ለሚጠይቀው የአካባቢ ምርጫ ይህ ሥልጠና የሚኖረውን አስተዋፅዖ አብራርተዋል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ባካተተ መልኩ የምርጫ ጽንሰ ሐሳቦችና ተሞክሮዎችን እንዲሁም ቴክኒካዊ ክሕሎት ለማስጨበጥ ታስቦ የተዘጋጀው ሥልጠና፣ የቦርዱን ተልዕኮና ኃላፊነት ጨምሮ አጠቃላይ የምርጫ ዑደትን የዳሰሰ ነው። ሥልጠናው ቦርዱ ከዚህ ቀደም ሚያዝያ 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም የ6ተኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት አስመልክቶ ለባለ ድርሻ አካላት ባዘጋጀው ዐውደ-ጥናት ላይ የተገኙ ትምህርቶችንና ቢሻሻሉ ተብለው የተያዙ የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት አድርጓል። ከቅ/ጽ/ቤት የተወከሉት ኃላፊዎችና ባልደረቦች በሥራው ሂደት አጋጠሙን ያሏቸውን ተግዳሮቶች ባነሱበት መድረክ፣ እነዚህን ተግዳሮቶች መፍቻ መንገድ በባለሞያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ሥልጠና የመዝጊያውን ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ናቸው። ዋና ሰብሳቢዋ በንግግራቸው እንደ ተቋም ባለን ጥንካሬ ላይ ሣይሆን አሉብን በምንላቸው ክፍተቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።
ብርቱካን ሚደቅሳ ሥልጠናው የክልል ቅ/ጽ/ቤቶች ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ሥራዎች በተዋረድ ወደ ቅ/ጽ/ቤት የመሄዳቸው ጉዳይ አይቀሬ መሆኑንም በመጠቆም፤ ከአተገባበር ጋር ችግሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራውን አስፈላጊነት አስረድተዋል። የሕግ ማዕቀፍ ላይ የሚሰጠው ሥልጠና የክልል ቅ/ጽ/ቤቶችን በተሻለ ለማዋቀርም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው በንግግራቸው አመልክተዋል።