ድምፅ አሰጣጥ

በመራጮች ምዝገባ ወቅት ከተመዘገቡ ዜጎች በኃላ በቦርዱ በተወሰነው የድምፅ መስጫ ቀን የተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡  የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ 

የድምፅ አሰጣጥ ሂደት 

  • የድምፅ መስጠት ሂደት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይጀመራል፡፡
  • በዕለቱም መራጮች በምርጫ ጣቢያው ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ እከስ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ በመገኘት ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ፡፡ በነዚህ ሰዓታት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ያልተቋረጠ የድምፅ መስጠት ተግባር ይከናወናል፡፡
  • ማንኛውም መራጭ ዜጋ በምርጫ ጣቢያው በአካል በመገኘት በሙሉ ነፃነት ድምፅ ይሰጣል፡፡ 
  • ማንኛውም ዜጋ ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ከሚመርጠው እጩ አጠገብ ባለው ቦታ ማንኛውንም (ኤክስ፣ ራይት ወይም የጣት አሻራ) ምልክት በማድረግ ድምፁን ይሰጣል፡፡ 
  • ማንኛውም ድምፅ የሚሰጠው በሚስጥር ነው፡፡ ድምፅ ለመስጠት እገዛ የሚያስፈልጋቸው ድምፅ ሰጪ ዜጎች ድጋፍ የሚሰጣቸውን ሰው ይዘው የሚስጥር ድምፅ መስጫ ውስጥ መገኘት ይችላሉ፡፡ ድጋፍ ሰጪው መብቱ በህግ ያልተገደበ መሆን አለበት፡፡ 
  • ማንኛውም መራጭ ድምፅ መስጠት የሚችለው፦
    • በመራጭነት በተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ ላይ፣
    • የመራጮች መታወቂያ ካርድ ሲኖረው፣
    • በመራጮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲገኝ፣
    • እንዲሁም ድምፅ ያልሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡
  • ማንኛውም መራጭ ድምፅ ለመስጠት በተገኘበት ምርጫ ጣቢያ ላይ ይዞ የተገኘውን የማንነት መግለጫ ሰነዶች በጣቢያው ላይ በሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ድምፅ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ማጣራት ይችላሉ፡፡ 
  • አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን፣ ህጻናትን የያዙ ወላጆች እና ነፍሰ ጡሮች በምዝገባም ሆነ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
  • ድምፅ የተሰጠባቸው ወረቀቶች ከሚከተሉት በአንዱ ምክንያት ዋጋ አልባ ሊሆኑ ይችላሉ፦
    • የመራጩ ማንነት በስም የተገለፀ ከሆነ፣
    • ለምክር ቤቱ መምረጥ ከሚቻለው እጩዎች ቁጥር በላይ ምልክት የተደረገበት ከሆነ፣
    • መራጩ ማንን እንደመረጠ መለየት የሚያስቸግር ከሆነ፣
    • ሕጋዊ የድምፅ መስጫ ወረቀት ያልሆነ ወይም በምርጫ ጣቢያው ያልተሰራጨ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሆኖ ከተገኘ፡፡

በድምፅ መስጫ እለት ሊከበሩ የሚገባቸው ስነ-ምግባር መርሆዎች

  • ማንኛውም ሰው በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ዙሪያ ክልል ውስጥ በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ፣ የጦር መሣሪያ በመያዝ ወይም በሌላ በማናቸውም ፀጥታን በሚያደፈርስ አኳኋን መገኘት የለበትም፡፡
  • ማንኛውም ድምፅ ሰጪ ያልሆነ ሰው ያለእውቅና መታወቂያ ወደ ምርጫ ጣቢያው በመግባት ወይም በምርጫ ጣቢያው ግቢ ውስጥም ሆነ ውጭ የምርጫውን እንቅስቃሴ ማወክ ወይም ማደናቀፍ የለበትም፡፡
  • ድምፅ ሰጪው ድምፅ ከሰጠ በኋላ ምርጫ ጣቢያውን እና ከባቢውን ለቅቆ መሄድ ይኖርበታል፡፡