Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን ቅደም ተከተል የሚወሥነውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት አካሄደ ::

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር የጠቅላላ እና የድጋሚ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሶማሌ እና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ምርጫ የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚህም ተግባራት አንዱ የዕጩዎች ምዝገባ ሲሆን፤ በትላንትናው ዕለት ማለትም ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የተመዘገቡ ዕጩዎችን በድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚኖራቸውን የአደራደር ቅደም ተከተል የሚወሥነውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።

በዚህ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢን ጨምሮ ሁሉም የቦርድ አመራር አባላትና በምርጫው ላይ የሚሣተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዩች የተገኙ ሲሆን፤ ሥነ-ሥርዓቱም የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ተከፍቷል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 56 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ቦርዱ የሚያዘጋጀው የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች ፎቶ-ግራፍ፣ የዕጩ መለያ ምልክት፣ የዕጩዎች ሙሉ ስምና የፖለቲካ ፓርቲያቸው መጠሪያን አካቶ ሊይዝ እንደሚገባ መደንገጉን አውስተው ይኽ ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ተወዳዳሪ የግል ዕጩዎና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸው በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን አደራደር ቅደም ተከተል እንደሚወሥንና ቦርዱ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ ሲተገብረው የነበረ ዲሞክራሲያዊ፣ ግልጽ፤ ነፃና ፍትሃዊ የምርጫ ሥርዓትን ከሚያረጋግጥባቸው ተግባራት አንዱ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ በሌላ በኩልም ቦርዱ በዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ለግል ዕጩዎና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ማድረጉን አስታውሰው በጥሪው መሰረት ካልተገኙ የዕጣ አወጣት ሥርዓቱ እንደሚቀጥል አስረድተዋል:: በመጨረሻም በዕጣ ማውጣቱ ለሚኖራቸው ዕድል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

Share this post