Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከታዛቢ ሲቪል ማኅበራት እና የሰብአዊ መብቶች ተከታታይ ድርጅቶች ጋር በተያዘው ዓመት የሚካሄደው ምርጫን አስመልክቶ ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ለሚያከናውነው የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ቀሪና የድጋሚ ምርጫን አስመልክቶ ጊዜያዊ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ይኽንንም ተከትሎ ቦርዱ የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከታዛቢ ሲቪል ማኅበራት እና የሰብአዊ መብቶች ተከታታይ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የቦርዱ የኦፕሬሽን የሥራ ክፍል፣ የሥርዓተ ፆታና አካታችነት የሥራ ክፍል እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና የአጋርነት ማጎልበቻ የሥራ ክፍል ምርጫውን የተመለከተ አጠቃላይ ገለጻ ለታዛቢዎቹ ያደረጉ ሲሆን፤ ይኽንንም ተከትሎ ከተሣታፊዎቹ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነሥተዋል። ተሣታፊዎቹ የቅድመ ምርጫ ገለጻው ስለምርጫው አጠቃላይ ምሥል በመስጠትና ዕቅዶቻቸውን ለአፈጻጸም ምቹ በሆነ ሁኔታ ለማዘጋጀት እንደሚረዳቸው የገለጹ ሲሆን፤ ባንጻሩ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ዳግም እንዳያጋጥሙ መወሰድ ያለባቸውን የዕርምት ዕርምጃ አጽንዖት ሰጥተው አስረድተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ የፀጥታ ጉዳይን፣ የፋይናንስ ውሥንነትን፣ የሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ አካታችነትን አስመልክቶ ያላቸውን ሥጋትና አስተያየት ጭምር ገልጸዋል።

የተሣታፊዎቹን አስተያየት ተከትሎ የቦርድ አመራር አባል በሆኑት ብዙወርቅ ከተተ እንዲሁም ከላይ በተጠቀሱት የሥራ ክፍሎች ተወካዮች አማካኝነት ለተጠየቁት ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል። የውይይቱን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የቦርድ አመራሯ ብዙወርቅ፤ የምርጫውን ሂደት የተመለከተ መረጃዎች ለተሣታፊዎቹ የማጋራቱ ሥራ እንደሚቀጥልና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲሁ በአካል በመገናኘት ተከታታይ ውይይቶች እንደሚደረጉ አስገንዝበዋል። በንግግራቸውም መጨረሻ እንኳን ለዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን አደረሰን ሲሉ በጎ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

Share this post