Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ስልጠና እና የእውቅና ምስክር ወረቀት ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚሠሩ 40 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ከ ጥር 29 እስከ ጥር 30 ቀን 2016ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ቀናት የቆየ የስልጠና መድረክ አዘጋጀ። መድረኩ በምርጫ ቦርድ አመራር አባል ዶ/ር አበራ ደገፋ የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን በመክፈቻ ንግግራቸው የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን በቋሚነት የመስጠትን ጠቀሜታ ካብራሩ በኋላ ይህ እንዲሳካ ከቦርዱ ባልተናነሰ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ዋነኛ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።

ስልጠናው የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ይዘትን ባካተተውና በቦርዱ በተዘጋጀው ማስተማሪያ እና የአሰልጣኞች መምሪያ (ማኑዋል) ላይ በተመለከተው መሰረት ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፥ የሕዝብ ውክልና ተቋማት በኢትዮጵያ፥ የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት እና የመንግሥት አወቃቀር፥ ስልጣን እና ተግባር፥ መንግሥት እና የፖለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ፥ ምርጫ-የምርጫ ሕግጋት እና የምርጫ ሒደቶች በኢትዮጵያ፥ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የዜጎች መብቶች እና ኃላፊነቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የሲቪል ማህረሰብ ተቋማቱ ትምህርት ከመስጠታቸው በፊት እንዴት የፍላጎት ምዘና (የዳሰሳ ጥናት) ማድረግ እንዳለባቸው፥ ለየትኛው የማህበረሰብ ክፍል በምን መልኩ መልዕክት መተላለፍ እንዳለበት፥ እንዲሁም የባለ ድርሻ ኣካላት አመራረጥን አስመልክቶ ስልጠና ተሰጥቷል።

የስነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን ለማሳካት የበጎ አድራጎት/የፈቃደኝነት ሥራ ያለው ሚና በቦርዱ የስነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል የተብራራ ሲሆን ተሳታፊዎች በቀጣይ በአካባቢያቸው የሚገኙትን ወጣቶችን እንዴት በበጎ ፈቃደኝነት ማሳተፍ እንደሚችሉ እና ወደፊትም በምርጫ ሂደቱ በተለያየ ደረጃ የሚያገለግሉ ወጣቶችን በምን መልኩ ማብቃት እንደሚቻል አጠር ያለ ማብራሪያ እና የሌሎች አገራት ልምድ በተመለከተ በስልጠናው ወቅት ቀርቧል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ቦርዱ በተናጠል እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በጋራ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት እና ለወደፊት የታቀዱ ሥራዎችን እንዲሁም የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን የሚሰጡ አካላት ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶችን በተመለከተም ገለጻ ተደርጓል።

በስልጠናው ወቅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ግንዛቤ ለማስፋት የቦርዱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ከስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። በዚህ መሰረት፡ የቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል በምርጫ ሕጉ ማዕቀፍ እና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳታፊነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳዮች ሥራ ክፍል በኩል ደግሞ ፓርቲዎች በመራጮች ትምህርት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈረመው ሰነድ እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የሚከናወን መሆኑን እና ለዚህም የሚውል ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት የሚሰጥ በጀት መኖሩን አስረድተዋል። ለወደፊቱም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት በመስራት የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ያለምንም መድሎ በገለልተኝነት ለህብረተሰቡ የሚሰጥበትን ዘዴ መተለም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የስርዓተ ጾታና አካታችነት ትምህርት ሥራ ክፍል በበኩሉ የሲቪል ማህበራቱ የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊስተናገዱ የሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ሴቶችን፥ የአካል ጉዳተኞችን፥ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በምን መልኩ በስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት አሰጣጥ ውስጥ ማካተት እንዳለባቸው አብራርተዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችም ከስርዓተ ጾታና አካታችነት ትምህርት ሥራ ክፍል የቀረበውን ማብራሪያ እንደ መነሻ በመውሰድ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የሰው ሀይል፣ የቁሳቁስ፣ የማስተማሪያ ዘዴዎችና እና ሌሎች ግብአቶችን ምንነትና እና የግብአቶቹን አቅርቦት በተመለከተ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

በቦርዱ የኮሙኒኬሽን ሥራ ክፍል ደግሞ መሰረታዊ የተግባቦት ክህሎቶችን በሚገባ መረዳት የስነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ከማስተላለፋችን በፊት ማዳበር የሚገባን ጉዳይ መሆኑን ካስረዱ በኋላ ይህንም ማሳካት የሚቻለው መልዕክቱን ለማሰተላለፍ የተመረጠውን ማህበረሰብ ከመረዳት እንደሚጀምር ገለጻ አድርገዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዝሃነት በሚንጸባረቅበት ማህበረሰብ ውስጥ የተለያዩ የተግባቦት ዘዴዎችን በመጠቀም የሚተላለፈው መልዕክት የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ለተሳታፊዎቹ የግንዘቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል፡፡ በቦርዱ የስልጠና ሥራ ክፍልም ስልጠና የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን ለማስረፅ ያለውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።

በሌላ መልኩም በመድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ከኢትዯጵያ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት በኩል በሰብአዊ መብትና የምርጫ ተያያዥነት እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ኃላፊነትን አስመልክቶ አጠር ያለ ገለጻ አድርገዋል።ይህም ማብራሪያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚወጡት ጭምር ከዳሰሳ ጥናትና ከልምድ የተገኘ ተሞክሮን አጋርቷል፡፡

ከተሳታፊዎች ጋር በተደረገው ዉይይትም የስልጠናው ተሳታፊዎቹ በስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት በቂ ግንዛቤ የጨበጡ መሆናቸው የተስተዋለ ሲሆን በስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ ትምህርቱ ለማን ተደራሽ መሆን እንዳለበትና እንዴት ሳይንሳዊ፣ ሳቢና ማራኪ በሆነ ዘዴ መሰጠት እንዳለበት በቂ ክህሎት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በትምህርት አሰጣጡ ዙሪያ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን እና ዋና ዋና ተግዳሮቶችን በማንሳት የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። በሌላም በኩል የመራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ማንዋል ላይ መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል። የቦርዱ ሊቀመንበር ክብርት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ለተዘጋጀው መድረክ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ካመሰገኑ በኋላ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን በዘላቂነት መስጠት ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ለዚህም ስኬት የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ዋነኛ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አፅንዖት በመስጠት የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። በመጨረሻም የቦርዱን መስፈርት ያሟሉ 40 የሲቪል ማህበራት ከክብርት ሊቀ መንበሯ የፍቃድ ምስክር ወረቀት ተቀብለው መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል።

Share this post