የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚያካሂደውን ሕዝበ ውሣኔ የመራጮች መዝገብ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዎላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሚካሄደው ሕዝበ ውሣኔ ከታኅሣሥ 11 እስከ ታኅሣሥ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያካሄድ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን ተከትሎ የመራጮችን መዝገብ ለአምስት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ክፍት አደረገ።
ቦርዱ የመራጮችን መዝገብ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ያደረገው ከዛሬ ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. (ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሳይጨምር) እስከ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ነው።
የተጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ፤ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ የመራጮች ምዝገባው በተሠረዘባቸውና በቦርዱ ውሣኔ በድጋሜ ከታኅሣሥ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. (ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሳይጨምር) እስከ ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የመራጮች ምዝገባ የሚካሄድባቸውን ምርጫ ጣቢያዎች አይጨምርም።