Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሣኔ በሚካሄድባቸው አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተፈጸሙ የሕግ ጥሠቶችን በተመለከተ የወሰዳቸው የዕርምት ዕርምጃዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያከሂደው ሕዝበ ውሣኔ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም የመራጮች ምዝገባ እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። ይህንንም የምዝገባ ሂደት ለመከታተትልና ለመቆጣጠር ከቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል የተዋቀረ ቡድን ከታኅሣሥ 16 - ታኅሣሥ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው የክትትል ሥራ፤ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች በሚገኙ ከታች በዝርዝሩ ላይ በተጠቀሱት የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች መፈጸማቸውን አረጋግጧል።

ቦርዱም የቀረበለትን ሪፖርት ተመልክቶ በተጠቃሾቹ ጣቢያዎች ላይ የተደረገው ምዝገባ እንዲሠረዝ ፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱም ሙሉ በሙሉ እንዲቆምና እንዲሁም የጣቢያዎቹ ሠራተኞች ከኃላፊነታቸው እንዲነሡ፣ በተጨማሪም ሁሉም የምርጫ ጣቢያው ሠራተኞች እና ግብር-አበሮቻቸው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው የወሠነ ሲሆን፤ የመራጮች ምዝገባውም አዲስ ሠራተኞች ተመልምለው በድጋሚ እንዲደረግ መመሪያ ሰጥቷል። በቀጣይም ቦርዱ ምዝገባውን ለማከናወን እና ያለፉትን የምዝገባ ቀናት ለማካካስ የሚያስፈልጉትን ተጨማሪ ቀናት እና ምዝገባው እንደገና የሚጀመርበትን ቀን የሚያሳውቅ ይሆናል።

የሕግ ጥሠቶች የተፈጸሙባቸው ጣቢያዎች እና የተፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት ዝርዝር

  1. በዎላይታ ዞን ዱቦ ምርጫ ጣቢያ ማንቴ ዱቦ የተፈጸመው ጥሠት፦ አቶ መሰለ ኤሊያስ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ፣ በተጨማሪም የቦርዱ ሠራተኛ ላልሆነ አቶ ወልዴ ወራጆ ለተባለ ግለሰብ ቁልፍ በመስጠት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ ማድረግ
  2. በዎላይታ ዞን ዶላ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ንዑስ ጣቢያ የተፈጸመው ጥሠት፦ አቶ አርጃ አሊሶ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ
  3. በዎላይታ ዞን ወርሙማ ምርጫ ጣቢያ ቤታሎ ለ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች ፊርማ ሳይፈርሙ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ማድረግ
  4. በዎላይታ ዞን ጫማ ሄምቤቾ ምርጫ ጣቢያ አምስት የተፈጸመው ጥሠት፦ በመዝገቡ ላይ ላልፈረሙ ግለሰቦች ካርድ መስጠት
  5. በዎላይታ ዞን ወርሙማ ምርጫ ጣቢያ ወርሙማ ሀ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ
  6. በዎላይታ ዞን ማንቴ ጌራራ ምርጫ ጣቢያ ማንቴ ጌራራ ሦስት የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ
  7. በዎላይታ ዞን ቶሜ ጌሬራ ምርጫ ጣቢያ ቶሜ ጌሬራ አራት የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ
  8. በዎላይታ ዞን ዋጭጋ ቡሻ ምርጫ ጣቢያ ዋጭጋ ቡሻ 02 የተፈጸመው ጥሠት፦ የመራጮች ፊርማ ሳይፈርሙ ግለሰቦች እንዲመዘገቡ እና ካርድ እንዲወስዱ ማድረግ
  9. ጎፋ ዞን ጃዉላ ጎሬ አዳ ምርጫ ጣቢያ የተፈጸመው ጥሠት፦ ተመሳሳይ የሆነ ወይንም በአንድ ሰው የተፈረመ በሚመስል ፊርማ ከአንድ በላይ ካርዶችን ወጪ ማድረግ
  10. ጎፋ ዞን ጃዉላ ውጋ መሸተላ ምርጫ ጣቢያ ሀ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች የመራጮች መዝገብ ላይ ሳይፈርሙ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ማድረጋቸው ይጠቀሳሉ።

ስለሆነም ቦርዱ በቀጣይም የክትትል ሥራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ማንኛውም ተመሳሳይ ተግባራት ሲከናወኑ ያየ ግለሰብ በነፃ ስልክ መስመር 778 ላይ ደውሎ ጥቆማውን ማቅረብ እንደሚችል ቦርዱ ያሳውቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም.

Share this post