የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አካሄደ፣ የተለያዩ ውሳኔዎችንም አስተላለፈ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ያደረገ ሲሆን ምክክሩም ፓርቲዎች በማስከተል (ከምርጫ ማግስት) ሊያሟሏቸው ስለሚገባቸው መስፈርቶች፣ ከመንግስት ስለሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እና እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ስላጋጠማቸው ገደቦች ያካተተ ነበር፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሰቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በተመራው ይህ ውይይት ላይ በቦርዱ ተመዝግበው የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል።
ለፓርቲዎች ከመንግስት ስለተሰጠው ድጋፍ እና ድጋፉን አስመልክቶ ማቅረብ ስለሚገባው ሪፓርት ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ስለጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ላይ ስላጋጠሟቸው ችግሮች ምክክር ተደርጓል።
በመሆኑም ምክክሩን ተከትሎ ቦርዱ የሚከተሉት ውሳኔዎችን አስተላልፏል፤
1. ከፓርቲዎች የሚጠበቀውን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ ከዚህ በፊት ቦርዱ ባስተላለፈው ውሳኔ አጠቃላይ ምርጫ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም ጠቅላላ ጉባኤ ያላከናወኑ ፓርቲዎች እንዲያከናውኑ የወሰነ መሆኑ ይታወሳል፣ በዚህም መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ያከናወኑ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ በአብዛኛው ፓርቲዎች ግን ጉባኤያቸውን አላደረጉም ይህንንም ተከትሎ ቦርዱ አሁን በተግባር ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ፓርቲዎች ጉባኤያቸውን አከናውነው እንዲያሳወቁ፤
2. ከመንግስት የተሰጠ የገንዘብ ድጋፍ የወሰዱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ያለፈውን የበጀት አመት ኦዲት ሪፓርት እንዲሁም አሁን የምንገኝበትን የበጀት አመት ደግሞ የሂሳብ ሪፓርት ለቦርዱ እንዲያቀርቡ የተወሰነ ሲሆን ፓርቲዎች ተጨማሪ ቴክኒካዊ ድጋፍ ከፈለጉ የፓለቲካ ፓርቲዎች የስራ ክፍልን መጠየቅ የሚችሉ መሆኑን ቦርዱ በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ ይወዳል ።