የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀን መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥር ፌደም/አፈ/11/61 በተጻፈ ደብዳቤ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ማለትም ኮንታ ልዮ ወረዳ፣ በምእራብ ኦሞ ዞን፣ቤንች ሸኮ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ ካፋ ዞን እና በሻካ ዞን በጋራ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በማቅረባቸው እና ቦርዱም ይህንን እንዲያስፈጽም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበለት በመሆኑ ቦርዱም ህዝበውሳኔው ውጤት የሚለካበትን መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ በመጠየቅ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በህዝቡ የተሰጠው ድምጽ አንድ ላይ ተዳምሮ የህዝበውሳኔ ውጤት የሚቀርብ መሆኑን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የህዝበውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ተከናውኗል።

የህዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ እና ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ህዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ እለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከነዚህ ስራዎች መካከልም የህዝበውሳኔውን በጀት ማዘጋጀት፣ የህዝበውሳኔው የሚከናወንበትን ጊዜ መወሰን፣ የተለያዩ ውይይቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ማከናወን፣ የአፈጻጸም ስልጠናዎችን መስጠት፣ የመራጮች መረጃዎችን ማድረስ ይገኙበታል።

በቅድመ ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት የቦርዱ ባለሞያዎች መረጃዎችን አደራጅተው እና ህዝበውሳኔው የሚከናወንባቸው ምርጫ ጣቢያዎች እና ምርጫ ክልልሎችን የመለየት ተግባራትም ተከናውነዋል። በዚህም መሰረት በ22 ምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 1613 ምርጫ ጣቢያዎች የህዝበውሳኔው የመራጮች ምዝገባ እና የመራጮች ድምጽ አሰጣጥ ተከናውኖባቸዋል። ከበጀት ቁጠባ፣ ከአፈጻጸም ቅልጥፍና እና ከጊዜ አንጻር ቦርዱ ህዝበ ውሳኔው ከ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር እንዲከናወን ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን የ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚከናወንበት ቀን መቀየሩን ተከትሎ የህዝበውሳኔው የሚከናወንበት ቀን ተለወጠ።

ህዝበውሳኔውን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ፣ም በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ጋር በጋራ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በህዝበውሳኔው ውስጥ ከሚካተቱ ዞኖች መካከል የመራጮች ምዝገባ [በትክክል] ያልተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎች በመኖራቸው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ለመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲዛወር ተደርጓል። በዚህም መሰረት አጠቃላይ ምርጫ ለማከናወን ቦርዱ ከተጠቀመው በጀት ውስጥ 7 ሚልዮን ብር በጀት ከህዝበውሳኔ ጋር ለተገናኙ ስራዎች ውሏል የሚል ግምት ተይዟል።

የህዝብ ወሳኔውን አፈጻጸም በሰላም ለማከናወን ይቻል ዘንድ ቦርዱ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አስተዳደር፣ህዝበ ውሳኔው ከሚከናወንባቸው ዞኖች አስተዳደሮች ጋር በትብብር ሰርቷል። በዚህም መሰረት ከህዝበውሳኔው አስተባባሪ ፕሮጄክት ቢሮ ጋር በመተባበር የምልክት መረጣ ስራ ተጠናቆ የህዝበውሳኔውን ድምጽ መስጫ ወረቀት ዝግጅት ተከናውኗል።

ቦርዱ በሁለት ዙር ስልጠና የወሰዱ ህዝበ ውሳኔውን የሚያስፈፅሙ 4427 አስፈፃሚዎችን የተሳተፈ ሲሆን፣ እነዚህም አስፈጻሚዎች የመራጮች ምዝገባ እና የህዝበውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ቀን የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል።

ለደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ከ መጋቢት 18 እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ፣ በልዮ ሁኔታ ደግሞ ከነሃሴ 26 እስከ ጷግሜ 06 ቀን ድረስ በአንድ ዞን ላይ ሁለተኛ ዙር መራጮች ምዝገባ ተከናውኗል፣ በዚህም መሰረት 1,344,622 ያህል ዜጎች በህዝበውሳኔው በመራጭነት ለመሳተፍ ተመዝግበዋል።

የድምጽ ሰጪዎች ለህዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ የሚያስችል ቅስቀሳ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ መልእክቶች ተላልፈዋል፡፡ ይህ የመራጮች ምዝገባ መልእክት ከአጠቃላይ ምርጫ መረጃ ጋር በጋራ የተላለፈ ሲሆን ለድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ደሞ በልዩ ሁኔታ የሚረዱ ለህዝበውሳኔው ተብለው በተዘጋጁ መልእክቶች እና ቋንቋዎች እንዲተላለፉ ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ህዝበውሳኔው የሚካሄድባቸው ዞኖች የመንገድ ላይ ቅስቀሳ በቦርዱ የመራጮች ትምህርት የስራ ክፍል አማካኝነት ተከናውኗል።

የህዝበውሳኔውን አፈጻጸም እና የጊዜ ሰሌዳ አስመልክቶ የአምስቱ ዞኖች እና የአንድ ልዩ ወረዳ አመራሮች ፣ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከህዝበውሳኔ ፕሮጄክት ቢሮ ጋር ከ5 ጊዜ በላይ ውይይቶች ተከናውነዋል፣ ከዚህም በተጨማሪ ህዝበውሳኔው የመጨረሻ አፈጻጸምን አስመልክቶ ሃዋሳ ከተማ ላይ ተጨማሪ ውይይት ተካሄዷል። ህዝበውሳኔው ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር በጋራ መከናወኑ በሰጠው ልዩ እድል በአካባቢው የህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የነጻ አየር ሰአት ድልድል የነበራቸው ሲሆን መታወቂያ የወሰዱ ወኪሎቻቸውም ሂደቱን እንዲታዘቡ ተፈቅዶላቸዋል።

የህዝበውሳኔውን ቁሳቁስ ዝግጅት እና ስርጭት ከአጠቃላይ ምርጫ ጋር በመከናወኑ የቁሳቁሶች ግዥ አብሮ የተከናወነ ሲሆን ለህዝበውሳኔው 1,774,500 ያህል የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ከአገር ውጪ ታትመው ተሰራጭተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የውጤት ማረጋገጫ ቅጾች እና ሌሎች ለድምጽ አሰጣጥ የሚረዱ ቁሳቁሶች በምርጫ ጣቢያዎቹ በተገቢው ጊዜ ደርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝበውሳኔ ማስተባበሪያ ጊዜያዊ ቢሮ በቦንጋ ከተማ የከፈተ ሲሆን ቢሮው ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የማስተባበር ስራን በማከናውን እንዲሁም የውጤት ድመራን የማጠናቀቅ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል።

መስከረም 20 ቀን 2014 ቀን የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች በመኖራቸው ደምጽ አሰጣጡ ለ2 ሰአታት ያህል ከመራዘሙ በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ በእለቱ የቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን ዴስክ ለሚጋጥሙ ችግሮች መፍትሄዎችን እየሰጡ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በቦንጋ ጊዜያዊ ቢሮ የሚያስተባብሩ የቦርዱ ሰራተኞችም ወደተለያዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በመንቀሳቀስ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ቀልጣፋ እንዲሆን አግዘዋል። በእለቱም 1,424 የሲቪል ማህበራት ታዛቢዎች በክልሉ ተሰማርተው ሂደቱን ታዝበዋል።

ድምጽ አሰጣጡ በአጠቃላይ ከተመዘገበው 1,344,622 መራጭ 1262679 ሰው ድምጹን ሰጥቷል፡፡ ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 93.9 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

በዚህም መሰረት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበውሳኔ የቀረቡት ሁለት አማራጮች ማለትም በኮንታ ልዮ ወረዳ፣ በምእራብ ኦሞ ዞን፣ቤንች ሸኮ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ በካፋ ዞን እና በሻካ ዞን በጋራ ክልል መመስረታቸውን ለመደገፍ ወይንም እነዚሁ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አስተዳደሮች የደቡብ ክልል አስተዳደር አካል ሆነው መቆየታቸውን ለመደገፍ በተደረገው ህዝበውሳኔ ውጤት በቦርዱ ተረጋግጧል።

በቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/ 2011 እንዲሁም በምርጫ ፓለቲካ ፓርቲዎች እና ስነምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 06 መሰረት በተከናወነው ህዝበውሳኔ በኮንታ ልዮ ወረዳ፣ በምእራብ ኦሞ ዞን፣ቤንች ሸኮ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ በካፋ ዞን እና በሻካ ዞን በጋራ ክልል መመስረታቸውን የሚደግፈው አማራጭ አብላጫ ድምጽ መደገፉ ተረጋግጧል፣ በዚህም መሰረት ቦርዱ ይህንኑ ውጤት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ ይሆናል።

ምስጋና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በክልልነት የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም ድጋፍ ያደረጉ የሚከተሉ አካላትን ምስጋና ያቀርባል።

  • በህዝበውሳኔው ድምፅ ለሰጡ ዜጎች
  • ህዝበውሳኔውን በተለያየ ደረጃ ላስፈጸሙ የምርጫ አስፈጻሚዎች
  • ለደቡብ ብሔርብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መስተዳደር
  • ለኮንታ ልዮ ወረዳ፣ ለምእራብ ኦሞ ዞን፣ለቤንች ሸኮ ዞን፣ ለዳውሮ ዞን፣ ካፋ ዞን እና ለሻካ ዞን መስተዳድሮች
  • ለደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበውሳኔ ማስተባበሪያ ፕሮጄክት ጽህፈት ቤት
  • ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰራተኞች
  • ህዝበውሳኔውን ሂደት ለታዘቡ እና በመራጮች ትምህርት ላይ ለተሳተፉ የሲቪክ ማህበራት
  • የህዝበውሳኔውን ሂደት ለዘገቡ ሚዲያዎች እና በየደረጃው ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ።

ማስታወሻ

የህዝበውሳኔው ዝርዝር ውጤት ከስር ተያይዟል።

ffff