የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምፅ መስጠት ሂደት ጋር ተያይዞ አቤቱታ ካቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ተሣትፈው በድምፅ መስጠት ሂደቱ ላይ አቤቱታ ካቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ በተገኙበት የተከናወነው የምክክር መድረክ፤ በፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን መፍትሔ ለመስጠት ቦርዱ በሚከተለው ሥርዓት ላይ ካለው ጊዜ አንጻር ፓርቲዎቹ ፈጣንና የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል ያሏቸውን የማዳበሪያ ሃሳቦች እንዲያጋሩ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ሲሆን፤ ይህንንም የቦርዱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ በንግግራቸው ገልጸውታል። የቦርዱ የህግ ክፍል ሃላፊም በምክክሩ የተገኙ ሲሆን አቤቱታዎች ሊኖራቸው የሚገባውን ቴክኒካል ይዘት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቦርዱ ከቀናት በፊት ፓለቲካ ፓርቲዎቹ አቤቱታዎቻቸውን የሚያቀርቡበትን የመረጃ አቀራረብ ቅደም ተከተል ገምግሞ የትኞቹ ጉዳዮች አቤቱታ የሚቀርብባቸው እንደሆኑ እንዲሁም በምን መንገድ መቅረብ እንዳለባቸው በይፋ መግለጹ ይታወቃል። ምክትል ሰብሳቢው በንግግራቸው ቦርዱ አቤቱታዎችን ለማደራጀትና ፓርቲዎቹ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁትን የመፍትሔ ሃሳቦች ሥርዓቱን ተከትሎ አደራጅቶ ለቦርዱ የሚያቀርብ የሕግ ባለሞያዎች ቡድን እንዳቋቋመ ገልጸው፤ አካሄዱን ይረዳል ያሉትን ተጨማሪ ሃሳብ እንዲያቀርቡ መድረኩን ቅሬታ ላስገቡት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ክፍት አድርገዋል።
ተሣታፊዎቹ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ የፓርቲዎቹን ሃሳብ ለመስማት መድረክ ማዘጋጀቱን፤ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ያልነበረ ተሞክሮ ነው በማለት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ሂደቱን ያግዛል ያሉትን የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦች አጋርተዋል። በዚህም መሰረት ቦርዱ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያመቸው ዘንድ ተመሳሳይ ስታንዳርድ ያለው የአቤቱታ ፎርም በማዘጋጀት እና የፓርቲዎችን አቤቱታ ከሚቀበሉ የህግ ባለሞያዎችን በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።