የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ማመልከቻ ላስገቡ እና በመጀመሪያ ዙር ላለፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁለት ቀናት ማለትም የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. እና የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. 6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ማመልከቻ ላስገቡ እና በመጀመሪያ ዙር ላለፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥልጠና ሰጠ። በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የተከፈተው መድረክ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ በቦርዱ የፕሮግራም ባለሙያ-የውጭ ግንኙነት ክፍል፣ በቦርዱ የሥርዓተ -ፆታ እና አካታችነት ክፍል እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያ ቀርቧል። ሥልጠናውን ለምን መስጠት እንዳስፈለገ የተናገሩት የቦርድ አመራሯ ብዙወርቅ ከተተ፤ የተወሠኑት ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ያስገቡት ሠነድ ላይ የዕቅድ አወጣጥና ዘዴ ክፍተት በመታየቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለምን ምርጫ መታዘብ ያስፈልጋል፣ የምርጫ መታዘብ ዕሴቶችና ጥቅሞች፣ በምርጫ መታዘብ ወቅት የሚጠበቁ የሥነ-ምግባር ደንቦችና ኃላፊነቶች፣ አካታችነትን ያማከለ የምርጫ መታዘብ ሂደት፣ የምርጫ መታዘብ አቀራረብ ዘዴ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች፤ ማለትም የምርጫ መታዘብ ስልት፣ ሪፖርቶችን ማደራጀት፣ የአካታችነት መርሆችን ተግባራዊ ማድረግ ከሥልጠናው ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ ሲሆኑ፤ የቀረበውን ሥልጠና የተመለከተ ውይይት ከተሣታፊዎች ጋር ተደርጎ የፕሮግራሙ ማብቂያ ሆኗል።