Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን 6ተኛ አገራዊ የምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ታኅሣሥ 16 ቀን 2013 ዓ.ም የቦርዱ አመራሮችና ፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት የመጪውን 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ አጠቃላይ የተሠሩ ሥራዎችና በመሠራት ላይ ያሉትን ሥራዎች ይፋ አድርጓል። የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳና የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ አጠቃላይ የቦርዱ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስልና የመጪውን ምርጫ ሂደት የተቀላጠፈና የዘመነ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ፤ በሂደቱም የነበሩት ተግዳሮቶች በዝርዝር አቅርበዋል። ቦርዱ መመሪያዎቹን አካታች ለማድረግም ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እንደሠራባቸው ያስገነዘበ ሲሆን ቦርዱ በአጠቃላይ እንቀስቃሴዎቹ በሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ተስፋ የሚቆርጥ ሣይሆን የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝቧል።

የቦርዱ አመራሮችን ማብራሪያ ተከትሎ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ክፍት የተደረገው መድረክ አበረታች ከሚባሉት አስተያየቶች አንስቶ ፓርቲዎቹ አሉብን እስካሏቸው ሥጋቶች ተስተናግደውባቸዋል። በምላሹም የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ሥጋቶቹ መሠረት እንዳላቸውና ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ በኩል የቀረቡትን ተስፋና ሥጋቶች እንደሚጋራ ነገር ግን የምርጫው ስኬታማነት ማረጋገጥ የሚቻለው በቦርዱ የብቻ ጥረት ብቻ ሣይሆን በጋራ በሚሠሩ የቅንጅት ሥራዎች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የምርጫ ቦርዱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማዘመን የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በቦርዱ የኦፕሬሽን ባለሞያዎች በምስል የታገዘ ማብራሪያ የተሰጠበት ሲሆን፤ የቦርዱ ዲጂታላይዝ መሆን ሂደቱን ምን መልክ እንደሚሰጠው ግንዛቤ ተሰጥቶበታል። አያይዞም የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ይኽውም የድምጽ መስጫው ቀን፤ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሣኔ ድምፅ መስጫን ጨምሮ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ሲደረግ፤ የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ መስተዳደሮች ድምፅ መስጫ ቀን ሰኔ 05 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሆን ተወሥኗል። ትግራይ ክልልን በተመለከተም የሁኔታዎች አመቺነት ታይቶ የጊዜ ሠሌዳ እንደሚወጣለት ተገልጿል። በማስከተልም በባለሞያዎች በቀረቡት ማበራሪያዎች ላይ ፓርቲዎቹ አለን ያሉትን ቴክኒካዊ ጥያቄዎችና አጠቃላይ ሁለተኛ ዙር ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤በቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳና በባለሞያዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸው የመድረኩ ማብቂያ ሆኗል። በፕሮግራሙ መዝጊያ ንግግራቸው ብርቱካን ፓርቲዎቹ ለሚኖሯቸው ማንኛውም ጥያቄዎች በቀጥታ በመቅረብም ሆነ በኢሜል ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቦርዱ ሁሌም ዝገጁ ነው ብለዋል።

election/calendar

 

Share this post