የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በረቂቅ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ- ፆታ ኦዲት ሠነድ ላይ የምክክር መድረክ አዘጋጀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት በረቂቅ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ- ፆታ ኦዲት ሠነድ ላይ ግብዓት ለመሰባሰብ የሚያስችለውን መድረክ፤ ሁሉም የቦርዱ አመራሮች እንዲሁም የፓለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት አካሂዷል። መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሠብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ኦዲቱ ያለንበትን የምናውቅበት ብቻ ሣይሆን ለምን እዛ ሆንን ብለን የምንጠይቅበት ጭምር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የሠነዱን ዝርዝር ሪፖርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ- ፆታና የሕግ ረ/ፕሮፌሰር የሆኑት እመዛት መንገሻ ያቀረቡት ሲሆን፤ ጥናቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የመልሶ ምዝገባ በፊት የነበሩትን ሠነዶች በግብዕትነት ተጠቅሟል። ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ቁጥር፤ እንዲኹም ውክልናቸውና መሠል መረጃዎቹ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መልሶ ምዝገባ በኋላ የቁጥር ለውጥ ሊያሳዩ የሚችሉበት ዕድል ቢኖርም አብዛኛዎቹ ግኝቶችም ሆኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላትና ከባለድርሻ አካላት የተወሰዱት አስተያየቶች ታማኝነት ያላቸው ናቸው ሲሉ ገልጸል።
የቀረበውን የሠነድ ሪፖርት ተከትሎ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለና እመዛት መንገሻ መሪነት ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተስተናግደውበታል።
የኢትዮጲያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ