ነሐሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም.
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት በኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት መጠየቁ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቦርዱ አመራሮች ከተሟሉለት በኋላ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን በሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ቦርዱን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅቶች በዝርዝር አሳውቋል። በዚህም መሠረት ቦርዱ ለምክር ቤቱ በላከው ደብዳቤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ፦
1. በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሀዋሳ ከተማን አስመልክቶ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልላዊ መንግሥት መቋቋም የሚያረጋግጥ ቢሆን ከተማዋን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብቶችና ግንኙነቶች ከዚህም ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሰራር ዘርግቶ ለቦርዱ በጽሁፍ እንዲያሳውቅ፣
2. የሕዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደህንነት ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል የክልል እና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች የሥራ እቅድ አዘጋጅቶ ለቦርዱ እንዲያሳውቅ፣
3. የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃን በተመለከተ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ እንዲያዘጋጅና እንዲያሳውቅ መጠየቁ ይታወሳል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የክልል ምክር ቤት በበኩሉ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ምላሹን ለቦርዱ አቅርቧል። በምላሹም ክልሉ ካለበት ሁኔታና የሥራ ጫና አንጻር የሲዳማ ዞን ክልላዊ መንግሥት ሆኖ ቢቋቋም ከሀዋሳ ከተማ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ህጋዊ ማእቀፍና እና በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ አባላት ስለሚኖራቸው የመብት ጥበቃ ጊዜ ወስዶ መወያየት እንደሚገባው፣ ህግ ማውጣት ድረስ የሚደርስ ሥራ መሆኑን ህግ ማውጣት ደግሞ፣ ማርቀቅ፣ ሕዝብ አስተያየት መሰብሰብ እንዲሁም ማጽደቅን የሚጨምር ሥራ በመሆኑ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ክልሉ በኮማንድ ፓስት ስር የሚተዳደር በመሆኑ የተጠቀሱት የአሰራርና የህግ ማእቀፎችን የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለማቅረብ ተለዋጭ ጊዜ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል። በዚህም መሠረት ቦርዱ የተለያዩ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ምክር ቤቱ ምላሹን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንዲያሳውቅ በሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት በነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ሕዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልል መሆን ቢያረጋግጥ የሀዋሳ ከተማን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት ስለሚኖራቸው ግንኙነትና የሃብት ክፍፍል ህግ ለማውጣትና ህጋዊ ማእቀፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰብ አባላትን ስለሚኖራቸው መብትና ጥበቃ ከህገ መንግሥቱ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፎችን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚያስፈልግ አሁን ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ ነገር ግን ከሕዝበ ውሳኔው አስቀድሞ የህግ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎቹን በማጽደቅ እንደሚያቀርብ አረጋግጧል።
በመሆኑም ቦርዱ ባደረገው ውይይት የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች አስተላልፎ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል።
1. ቦርዱ ከነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ የሕዝበ ውሳኔውን የድርጊት መርሃ ግብር እና በጀት አዘጋጅቶ ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ለሚመለከታቸው አካላት የላከ ሲሆን በእቅዱ መሠረት የሕዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫ ቀን ኅዳር 03 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሆናል።
2. ቦርዱም በድርጊት መርሃ ግብሩ መሠረት፣ የባለድርሻ አካላትን ማስተባበር እና የአፈጻጸም ውይይት የማድረግ ስራውን ከነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ሳምንታት የሚያከናውን ሲሆን ከዚህም ተጨማሪ የ8,460 (ስምንት ሺህ አራት መቶ ስልሳ) ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል 1,692 (አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ማደራጀት፣ የሕዝበ ውሳኔ መመሪያዎች የማውጣትና የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የመሳሰሉትን ስራዎች ያከናውናል።
3. ቦርዱ በተጨማሪም ከመስከረም 07 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሕዝበ ውሳኔውን ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የእቅድ ዝግጅት ለማከናወን ከፌደራል፣ ከክልል እና ከዞን የጸጥታ አካላት ጋር የጋራ እቅድ የማውጣት ውይይቶችን ያደርጋል።
4. የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳን ከተማ የወደፊት ሁኔታ፤ የሃብት ክፍፍል እና የሌሎች ብሔረሰብ አባላትን የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎችን ማውጣት ሥራ እስከ መስከረም 22 ድረስ ያጠናቀቃል።
5. የደቡብ ብሔሮር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ቦርዱ ባቀረበው ዝርዝር የበጀት እቅድ መሠረት ሕዝበ ውሳኔን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን 75,615,015.00 (ሰባ አምስት ሚልዮን ስድስት መቶ አስራ አምስት ሺህ አስራ አምስት) ብር በጀት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ወደ ቦርዱ የባንክ አካውንት ያስተላልፋል።
በመሆኑም ቦርዱ የቴክኒክ ጉዳዮች በቀሪው ጊዜ ሲያጠናቅቅ ባለድርሻ አካላትም በተሰናዳው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ሕዝበ ውሳኔው በታቀደለት ጊዜ መሠረት እንዲከናወን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ያስታውቃል።