Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዓለም አቀፍ ችግር የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስጋት በምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ እንዲሁም ሊወሰዱ ስለሚችሉ አማራጭ እርምጃዎች ውይይት አከናውኗል

መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም.

የገዢው ፓርቲን ጨምሮ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለት የተለያየ ዙር በዚህ ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት የተሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለጥቂት ሳምንታት እንኳን ከቀጠለ በቀጣይ በዋናነት መፈጸም በሚገባቸው የመራጮች ትምህርት፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና፣ የቁሳቁስ ስርጭት ከፍተኛ የሰው ዝውውርን የሚያሳትፉ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ዝግጅት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኙ በዚሁ መልኩ ከቀጠለ የምርጫው ዝርዝር አፈጻጸም እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖዎችን እና ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምገማ ከፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተከታታይ እንደሚያደርግ አሳውቋል፡፡ 

ፖለቲካ ፓርቲዎችም በበኩላቸው ይህንን አገራዊ እና መንግሥት አቀፍ ችግር በምርጫ ሂደት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ እንደሚገነዘቡ ገልጸው መደረግ አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች ያጋሩ ሲሆን ከሁኔታዎች በፍጥነት ተለዋዋጭነት አንጻርም ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች እያገናዘበ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተደረገባቸው ውሳኔዎችን እየወሰነ መሄድ እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ቦርዱም የዛሬው ዓይነት ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያከናውን አሳውቋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post