የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲሱን አርማ ለሕዝብ ይፋ አደረገ
የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጲያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ የሚያደርገው ውይይት ከመስከረም 27 እና 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ከተደረገው የመጀመሪያው የባለድርሻ አካላት ኮንፈረንስ ቀጣይ ሲሆን የውይይቱም ዋና ዓላማ የመጪው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረግ፣ ስለ ምርጫ ቦርዱ የሥራ እንቅስቃሴዎች እና ስለ 2012 አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት መረጃ ማካፈል፣ የምርጫ ዋና ዋና ተሳታፊዎች እና የትብብር ኃላፊነቶች እንዲሁም ስለቦርዱ ሥራዎችን በተመለከተ ውይይት ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከታህሳስ ቀን 2011 ዓ.ም. አንስቶ የተለያዩ የህግ ማእቀፍ ማሻሻያዎችን እንዲሁም ድርጅታዊ መዋቅር ማሻሻያዎችን፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እና ክትትል የማድረግ ሥራዎችን፣ ከሲቪል ማህበራት በምርጫ ሥራው ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማበረታታት እና በአጋርነት ለመሥራት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተሻለ ትብብር ለመሥራት እና በሌሎችም ዘርፎች ብዙ ማሻሻያ እና ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
በዛሬውም ውይይት ላይ በዋናነት የሚነሱ ነጥቦች፡- ከምርጫ ቦርድ ሥራዎች ጋር የተገናኙ ህጋዊ ማእቀፍ እና መመሪያዎችን፣ ተቋማዊ ሪፎርም እና ተያያዥ ሥራዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዮች እና በ1162 መሠረት አዳዲስ መስፈርቶችን የሟሟያ ምዝገባን በተመለከተ፣ የኮሚዩኒኬሽን እና የውጭ ጉዳዮችን በተመለከተ፣ ምርጫ 2012 ዝግጅት እና ሰሌዳን በተመለከተ፣ ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የተገኙ ግብአቶች እንዲሁም ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የፀጥታ ጉዳዮች እና አለመግባባቶች አፈታት ሥርዓቶችን በተመለከተ ናቸው።