የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 27- 28 ያደረገው የሁለት ቀን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተጠናቀቀ
መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዩኤስኤድ እና ለዓለም አቀፍ የምርጫ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር “አገራዊ ምርጫ እና የምርጫ ባለድርሻ አካላት” በሚል ርእስ በምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያዘጋጀው የሁለት ቀን ኮንፍረንስ ተጠናቋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ከተለያዩ አገሮች የተጋበዙ እንግዶች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን በቀጣዩ ምርጫ ሊታሰብባቸው የሚገባ ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮችም ላይ ውይይት ተደርጓል። በክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጉባኤውን የከፈቱ ሲሆን መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አገርን በማስቀደም ለቀጣዮ ምርጫ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋእጾ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል። ሚዲያ፣ ሲቪል ማህበራት እና ዜጎችም ሰላምን ባስጠበቀ ግጭትን በማያስነሳ መልኩ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በመጀመሪያው ቀን የጉባኤው ውይይት የናይጄሪያ የቀድሞ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ፕሮፌሰር አታሩ ጄጋ የናይጄሪያን ልምድ ያካፈሉ ሲሆን ለሁለት የምርጫ ዙር ያስፈጸሙትን የተሳካ የምርጫ ሂደት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በናይጄሪያ የመጀመሪያውን በምርጫ እና በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የተላለፈበትን ምርጫ በመምራታቸው ያገኙትን ልምድ እንዲሁም በምርጫ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ሊያጋጥም የሚችለውንም ተግዳሮት እና መፍትሄዎች ገልጸዋል። ከተሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄም መልስ ሰጥተዋል። በማስከተልም ምርጫ “ማህበረሰባዊ ብዝሃነት ባላቸው አገራት” በሚል ርእስ ሥር ሁለት የምርጫ ባለሞያዎች ከተለያዩ አገራት የተገኙ ልምዶችን አካፍለዋል። ብዝሃነት ባላቸው አገራት የሚደረጉ ምርጫዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለባቸው ዋና ዋና ነገሮች በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመጀመሪያው ቀን የመጨረሻው የውይይቱ ክፍል አምስቱ የምርጫ ቦርድ አመራር አካላት ቦርዱ እየሠራቸው ያሉ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች እና ሌሎች የሪፎርም ሥራዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተነሱላቸውን ጥያቄዎችም መልስ ለመስጠት ሞክረዋል።
በሁለተኛው ቀን ጉባኤ የምርጫ ዝግጅትና የምርጫ ደህንነትን አስመልክቶ ቦርዱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያስጠናው ጥናት የቀረበ ሲሆን የግጭት ቅድመ ዝግጅት፣ መረጃ አሰባሰብና የምርጫ ተሳታፊዎች ደህንነት ላይ ውይይት ተደርጓል። በማስከተልም አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ መደረግ ያለባቸው ተግባራዊ መፍትሄዎች ላይ በሜጀር ጄነራል አለምሸት ደግፌ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፣ የመፍትሄ እርምጃዎችም ተጠቁመዋል። ከ200 የምርጫ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ይህ ገባኤ የተካሄው በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ነው።