Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህግ አስፈጻሚ የጸጥታ አካላት እና የቦርዱ የሥራ አመራር አባላት የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም ሰላማዊነት ማረጋገጥ አስመልክቶ መስከረም 07 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት አካሂደዋል

መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም.    

በውይይቱ የፌደራል ፓሊስ ተወካዮች፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ተወካዮች፣ በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ኃላፊ፣ የሀዋሳ ከተማ ፓሊስ አዛዥ፣ የሲዳማ ዞን ፓሊስ ኃላፊ የክልሉ የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ ተገኝተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ወቅት ቦርዱ ከዕለት ተዕለት ሰላምና ፀጥታ አጠባበቅ በተለየ የምርጫ ሂደት በራሱ የሚፈልገው የፀጥታ ዝግጅት መኖሩን ገልጾ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ፣ እንዲሁም የድምፅ መስጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ አስፈጻሚ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ለተሳታፊዎቹ አስገንዝቧል። ከተለያዩ ቢሮዎች የተወከሉት የጸጥታ አካላትም በነሱ በኩል ያለውን እይታ ያቀረቡ ሲሆን የዞኑ ሰላምና መረጋጋት እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸው በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና በጋራ እና በተናጠል ሊያከናውኗቸው ስለሚገቧቸው ተግባራትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በመጨረሻም በሂደቱ (በሕዝበ ውሳኔው ዝግጅት፣ ድምፅ አሰጣጥ እና ድህረ ሕዝበ ውሳኔው) ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን፣ መወሰድ ያለባቸው የመፍትሄ ተግባራትን እና ኃላፊነቱን የሚወስደውን አካል የሚያሳይ የሕዝበ ውሳኔ ፀጥታ እቅድ በስብሰባው ተሳታፊ በሆኑት የህግ አስፈጻሚዎች ተዘጋጅቶ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚደረገው ቀጣይ የጋራ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ ከስምምነት ተደርሷል። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከታው የባለ ድርሻ አካላት ላገኘው በጎ የትብብር መንፈስ ምስጋናውን ማቅረብ ይፈልጋል።

Share this post