የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔን አፈጻጸም አስመልክቶ ከክልልና ዞን ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ
ጳጉሜ 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔን አፈጻጸም አስመልክቶ የተለያዩ አካላት ጋር የሚደረጉ የተለያዩ ውይይቶችን እንደሚያከናውን ባስቀመጠው የድርጊት መርሃ ግብር መሠረት ነሐሴ 30 ቀን 2019 ዓ.ም. ከደቡብ ክልል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምክር ቤት ተወካዮች፣ የክልሉ አመራር አባላትና ከዞኑ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሒዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አፈጉባኤ ሄለን ደበበ፣ ምክትል አፈጉባኤ መንግሥቱ ሻንካ፣ የክልል መስተዳደር ጽ/ቤት ዋና አማካሪ አኒሳ መልኮ፣ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደስታ ሌዳሞ፣ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከቦርዱ አባላት ጋር ገንቢ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም ላይ፦
1. በተጠየቀው በጀት በኩል ምንም ዓይነት ችግር እንደማይኖር፣
2. በዞኑ የሚኖሩ እድሜያቸው ለመምረጥ የደረሰ ነዋሪዎች ሁሉ በሕዝበ ውሳኔው እንደሚሳተፉ፣ ክልሉም በበኩሉ ለምርጫ ቦርድ ሎጀስቲክስ ዝግጅት ለማቀላጠፍ በዞኑ ስር የሚገኙ ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄድባቸውን ቀበሌዎች ዝርዝር እንደሚያሳውቅ፣
3. የህግ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎቹን ማውጣት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ክልሉ ከመርሃግብሩ ከተጠቀሱት ቀናት ጥቂት ተጨምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ቦርዱ በማስከተል በመርሃ ግብሩ መሠረት ሌሎች ተመሳሳይ ውይይቶችን ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያከናውን ሲሆን በየጊዜው ሂደቱን የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡