Skip to main content

የፓለቲካ ፓርቲዎች የውይይት ርእሶችና ቅደም ተከተላቸው ላይ ከስምምነት ደረሱ

ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም.            

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተአማኒነት ያለው ተቋም ለመገንባት ካስተዋወቃቸው የተለያዩ ለውጦች መካከል አንደኛው የፓለቲካ ፓርቲዎች ውይይት (Political Parties Dialogue) አንዱ ነው፡፡ በቦርዱ አስተባባሪነት የሚካሄደው ውይይቱ የተለያዩ ውጤቶችን ያፈራ ሲሆን እስካሁን፦

  • የፓለቲካ ፓርቲዎች የቃልኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፣
  • የውይይት መምሪያ ህግጋት አውጥተው አጽድቀዋል፣
  • የጋራ ምክር ቤት መስርተው አመራሮችን መርጠዋል።

በዛሬው ዕለት ቀጥሎ በዋለው ውይይት የፓለቲካ ፓርቲዎች በማስከተል በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚያደርጓቸው ውይይቶች ርእሶችን እና አወያይ ግለሰቦችን ሲመርጡ ውለዋል፡፡ ፓለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ርእሶች እና የውይይት ቅደም ተከተላቸውን ቀድመው ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱ የቅደም ተከተሎቹን በማሰባሰብ የተለያዩ የቅደም ተከተል አማራጮችን በማጠናቀር ለውይይት አቅርቧቸዋል፡፡ በማስከተልም ባሉት አማራጮች ላይ የፓርቲ ተወካዩች በአንድ ቡድን 13 በመሆን የተወያዪ ሲሆን በውይይታቸው ማብቂያም ውይይት ሊረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ርእችሶች በቅደም ተከተል አቅርበዋል፡፡ በቅደም ተከተል የቀረቡ አማራጮች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የሚከተሉት ርእሶች ላይ በቅደም ተከተል ለመወያየት ፓርቲዎቹ በስምምነት ወስነዋል፡፡


1. የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይን በተመለከተ
• ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ፣
• ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ትብብር ጥምረት፣
• ያልተመዘገቡ ፓርቲዎች (ከውጭ ሀገር የመጡና በሀገር ውስጥ ያሉ)፣
2. ምርጫ ቦርድን በተመለከተ
• ስለ ምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣
• የምርጫ አፈፃፀም ሂደቱን ስለማዘመን፣
• የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት፣
3. ምርጫ 2012 እና የአካባቢ ምርጫ
• የምርጫ መራዘምን የሚመለከት፣
• የ2012 ጠቅላላ ምርጫ፣
• የአካባቢ ምርጫ፣
• ሰላምና መረጋጋት፣
• ስለሰብአዊ መብት፣
4. ህገ መንግሥት እና ፌደራሊዝም
• የህገ መንግሥት ማሻሻያ፣
• ፌዴራላዊ ስርዓቱ እና የሥራ ቋንቋ (ኦሮምኛን ከአማርኛ እኩል የሥራ ቋንቋ የማድረጉ ጉዳይ)፣
• የአዲስ አበባ ጉዳይ፣
• ሚዛናዊ ውክልና በሁሉም ደረጃ ስለ ማግኘት፣
• የማንነት ጥያቄዎች እና የወሰን ግጭቶች፣
• የክልሎች የውስጥ ግጭትን መንስኤ መመርመር፣
• ፌደራላዊ ሥርዓቱ እና የሀብት ክፍፍል፣
• የፌደራል ስርዓቱን ጠንካራና ደካማ ጎን መመርመር፣
• የመንግሥት አደረጃጀት፣
• የፌደራል ክልሎች አከላለል፣ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮች፣
• የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል የተመለከተ፣
• የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች አከላለል ጉዳይን መመርመር፣
• የፌደራል ከተሞች እና ነዋሪዎች ጉዳይ፣
5. የዴሞክራሲ ተቋማትን የማሻሻል ጉዳይን በተመለከተ
• የመገናኛ ብዙሀን ሕግ ማሻሻያ፣
• የፌደራል ሚድያ አገልግሎት አሰጣጥ መልክ ማስያዝ፣
• የመገናኛ ብዙሀን ገለልተኛነት እና አጠቃቀም፣
• የአቃቤ ህግ፣ የፖሊስ፣ የደህንነት እና የመከላከያ ተቋማት ግንባታን ስለማሻሻል፣
• የዳኝነት ሥርዓቱን ስለማሻሻል፣
6. ከአገራዊ መግባባት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች
• ሰንደቅ ዓላማ፣
• ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት፣
• የሕዝብ ቆጠራ፣
7. የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ
• ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስለሚደረግ ግንኙነት፣
በተጨማሪም የተለያዩ ገለልተኛ አወያይ ፍቃደኞች ቀርበው የተመረጡ ሲሆን በዚያም መሠረት የተመረጡት ግለሰቦችና ምሁራን ፍቃደኝነታቸው ላይ ተመስርቶ ውይይቶቹን የሚመሩ ይሆናል፡፡

Share this post