Skip to main content

ለፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማገዣ በሚል መንግሥት የመደበውን 10 ሚሊየን ብር ሥራ ላይ እንዳላዋለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ

ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም.   

ለፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማገዣ በሚል መንግሥት የመደበውን 10 ሚሊየን ብር ሥራ ላይ እንዳላዋለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ። ገንዘቡ ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ብቻ የሚጠቀምበት ይሆን ነበር። ፍትሃዊ ባልሆነ ምርጫ የምክር ቤቶችን ወንበር ሙሉ በሙሉ ለተቆጣጠረው ገዢው ፓርቲ ብቻ ገንዘቡን መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም ብሏል ምርጫ ቦርድ። የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መንግሥት ፓርቲዎችን ለማገዝ በሚል የሚመድበውን 10 ሚሊዮን ብር ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ውስጥ ባላቸው መቀመጫ ልክ ገንዘቡ ይከፋፈላል የሚል አሠራር ነበር።

የምክር ቤቶቹ ወንበር በገዢው ፓርቲ ብቻ እንደተያዘ እየታወቀም ገንዘቡን አውጥቶ ለዛ ፓርቲ ብቻ መስጠቱ ትርጉም ያለው ለውጥ ስለማያመጣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ይመለሳል ብለዋል ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን። ለፖለቲካ ፓርቲዎች የእለት ተእለት ሥራ ማገዣ በሚል በመንግስት የተመደበው 10 ሚሊየን ብር ለገንዘብ ሚኒስቴር ከተመለሰ በኋላም ምርጫ ቦርድ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ላለበት ሌላ ችግር ሥራ ላይ እንዲያውለው እንዲፈቀድለት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑንም ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በምርጫ ቦርድ ይሰጥ የነበረውን የሥነ ዜጋ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርቱ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራምን ያካተተ ስለነበር ተቀይሮ እንደ አዲስ እየተዘጋጀ መሆኑን ከሰብሳቢዋ ሰምተናል። ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ እንደ አዲስ ሥርዓተ ትምህርቱ እየተቀረፀ ነው ያሉት ወ/ሪት ብርቱኳን ትምህርቱ ማህበረሰቡ ከኖረበት ባህልና ከሚናገረው ቋንቋ ጋር በተስማማ መልኩ ተዘጋጅቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል። የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ እና ህብረተሰቡ ለቦርዱ ያለውን አመኔታ ለመመለስ ቦርዱ እንደ አዲስ እየተደራጀና ቦርዱን የተመለከቱ የተለያዩ ህጎችም እየተሻሻሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡" (ትዕግስት ዘሪሁን)

ማስታወሻ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ትላንትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ9 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፓርትን አቅርበዋል። በሪፓርቱም ቦርዱ የዕለት ተዕት ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪ የቦርዱን ተአማኒነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቁ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውን እና የሥራ አፈጻጸሙ የሚታይበት መንገድም ከሌሎች የተለመዱ ጊዜዎች የተለየ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

Share this post