Skip to main content

ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሁናዊ ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችንና መፍትሔዎቻቸውን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ

ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሁናዊ ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችንና መፍትሔዎቻቸውን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ጋር ተወያየ። የውይይቱን መክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የስብሰባው ዋና ዐላማ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እያደረጉ ባሉት ዝግጅት ላይ ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ለመወያየትና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲሁም ለድምፅ መስጫው ቀን በቀሩት ጥቂት ቀናት ከማን ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ ለመወያየት መሆኑን ተናግረዋል።

የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ተስፋዬ ንዋይ ቦርዱ በቅድመ-ምርጫ ተግባራቱ ያከናወናቸውንና በማከናወን ላይ ያላቸውን አጠቃላይ ሪፖርት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፤ ከነዚኽ ውስጥም በቴክኖሎጂ ስለታገዘው የምርጫው ሂደት፣ ስለዕጩዎች ምዝገባ፣ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሽ አጠቃቀም፣ የበጀት ድልድልን እና ነፃ የዓየር ሰዓት አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች መመሪያዎች ምርጫውን አስመልክቶ ስለመርቀቃቸው፣ መደበኛና የምርጫ በጀቱ የሚደለደልበት ቀመርን የተመለከቱት ይገኙበታል።

ሪፖርቱን ተከትሎ ከተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ አስተያየት የተሰጠ ሲሆን፤ ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥም ለምርጫ ቅስቀሳ የተደለደለው ገንዘብ ውሥንነት፣ በተወሠኑ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ ዕጩዎች ላይ የሚደርስ ማዋከብ፣ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላይ ያሉ አስፈጻሚዎች የደንብ መተላለፍ፣ የድምፅ መስጫ ቀን ይራዘም የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ሜላትወርቅ በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግራቸው ለተነሡት ጥያቄዎች ማብራሪያ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ በመጨረሻም ፓርቲዎች በቦርዱ ለሚጠየቁት መረጃ በወቅቱ መረጃውን ማቅረብ ለሥራው ቅልጥፍና ወሣኝ እንደሆነ፤ እንዲሁም በቻሉት መጠን ቅሬታዎቻቸውን በማስረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡ ቦርዱ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ለሚያደርገው ጥረት አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በተጨማሪም ቦርዱ የዲጂታል አማራጮችንም በመጠቀም ከፓርቲዎች ጋር የሚኖረውን የመረጃ ልውውጥ ለማቀላጠፍ እንደሚሠራ አሳውቀዋል።

Share this post