የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያቀረበው “ምርጫችን ነው - ሀገር ያለኛ” የተሰኘ ኅብረ ዝማሬ በይፋ አስመረቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሂደት የዜጎችን ተሣትፎን ለማበረታታት “ምርጫችን ነው -ሀገረ ያለኛ” የተሰኘ አዲስ የምርጫ ኅብረ ዝማሬ ዛሬ የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ አስመረቀ። የኅብረ ዝማሬው ዐላማ በዋናነት በምርጫ ሂደት ውስጥ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያላቸውን ተሣትፎ ማሳደግ፣ ዜጎች በምርጫው ወቅት መብትና ግዴታቸውን ተገንዝበው በንቃት እንዲሣተፉ ማነሳሳት እና ማበረታታት እንዲሁም የልዩ ልዩ ድምፆች ኅብራዊነት ያለውን የጋራ ጥንካሬ በማሳየት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አሣታፊነትንና አንድነትን ማጎልበት ነው።
የኅብረ ዝማሬውን ይፋ ማድረጊያ መድረክ በንግግር የከፈቱት ሜላትወርቅ፤ ቦርዱ ቀደም ሲል በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫም “የሀገር ካስማ” የሚል ኅብረ ዝማሬ ይፋ ማድረጉን አስታውሰው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም እንዲሁ “ምርጫችን ነው -ሀገረ ያለኛ” የሚል አዲስ ኅብረ ዝማሬን አካታች ተሣትፎን ለማበረታታት በማሰብ ይፋ እንዳደረገ ተናግረዋል።
ቦርዱ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ኅብረ ዝማሬ መርኅ-ግብሩ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ አምስቱም የቦርድ ሥራ አመራር አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው የዲሞክራቲክ ተቋማት ኃላፊዎች እና ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አካላት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።