Skip to main content

ቦርዱ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያደርግ የነበረውን ውይይት አጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም. 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ሲያደርግ የነበረውን የሁለት ቀናት ውይይት አጠናቀቀ። ቦርዱ በመጀመሪያ ቀን ውይይቱ ሀገር ዐቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ከከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች ጋር ያወያየ ሲሆን፤ በሁለተኛው ቀን ውይይቱ ደግሞ የክልል ዐቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አወያይቷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊው ብሩክ የወንደሰን በአረንጓዴ (ምንም ዓይነት ሥጋት የሌለበት)፣ በቢጫ (መጠነኛ ሥጋት ያለበት) እና በቀይ (አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት ያለበት) ተብለው የተፈረጁትን ቦርዱ ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት ያሰባሰበውን የምርጫ ክልሎችን አሁናዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የተመለከተ መረጃ በዝርዝር አስረድተዋል። ዝርዝር ማብራሪያውን ተከትሎ የውይይቱ ተሣታፊ የሆኑት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃሳብ አስተያየት ሰጥተዋል።

በውይይቱ የማጠቃለያ ንግግራቸው የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለውይይቱ ተሣታፊዎች ሃሳብ አስተያየታቸውን ስላጋሩ አመስግነው፤ በሰላምና ፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በምርጫ ኦፕሬሽንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ተከታታይነት ያላቸው ስብሰባዎች እንደሚኖሩ አስታውሰዋል። በመቀጠልም “ምርጫ” ምርጫ ቦርድ በሚያደርገው የብቻ ጥረት ብቻ ሣይሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ጭምር ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊነቱ እንደሚረጋገጥ በአፅንዖት ተናግረዋል።

Share this post