Skip to main content

ቦርዱ በምርጫ መታዘብ ለሚሳተፉ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የበይነ-መረብ ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብር አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለሚታዘቡ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች በበይነ-መረብ አማካኝነት ምዝገባ እንዲያደርጉ እና መረጃ እንዲያደራጁ የሚያስችላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብር ከጥቅምት 25-26 ቀን 2018 ዓ.ም. አካሄደ።

በበይነ-መረብ አማካኝነት የሚደረገው ምዝገባ እና የመረጃ አያያዝ ቀድሞ በተለምዷዊ ስርዓት ይከናወን የነበረውን አሰራር በዘመናዊ ስርዓት የቀየረ ነው። የግንዛቤ ማስጨበጫው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በበለጸገው የበይነ-መረብ መመዝገቢያ እና መረጃ መያዣው ላይ የራሳቸውን ግብዓት እንዲጨምሩበትም ያለመ ነው።

በበይነ-መረብ የሚደረገው ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ፤ የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ፣ በተገቢው ለመሰነድ እና የመረጃ ትንተና ለማዘጋጀት በእጅጉ ጠቃሚ እንደሆነ በመርሀግብሩ ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ እና በምርጫ ታዛቢነት የሚሳተፉ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥ የሚያቀላጥፍ፣ የጊዜንና ገንዘብ ብክነትን የሚቀንስ ነው። የመረጃ መዛባትን የሚቀንስ እንደሆነ የተነገረለት ይኽው የቴክኖሎጂ አማራጭ፤ በምርጫ መታዘብ የሚሳተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንም ቀደም ሲል ከሚስተዋለው እንግልት የሚታደጋቸው ነው።

የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፤ የበይነ መረብ መተግበርያው ታሳቢ ቢያደርጋቸው የሚሏቸውን ሀሳብ ያነሡ ሲሆን የቦርዱ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ-ግብሩ በታዚቢነት የሚሳተፉ 54 የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፤ የመራጮች እና እጩዎች መመዝገቢያን ጨምሮ፤ ቦርዱ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እያዘመነ የመጣው አሰራር የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫው በገጽ-ለገጽ እና በዌብናር አማካኘት የተካሄደ ነው።

Share this post