Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከናይጄሪያ አቻው Independent National Electoral Commission (INEC) ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ የምርጫ አፈጻጸምን ያዘምናሉ ያላቸውንና ነፃና ተዓማኒነቱን፤ አሣታፊና ተደራሽነቱን ለማጎልበት የሚያግዙትን በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚኽም ውስጥ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለአፈጻጸም አስቸጋሪና ተግባራዊ ለማድረግ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁነት ጋር መጣጣም ያልቻሉትን የሕግ ማዕቀፎች በባለሞያ አስጠንቶና ባለድርሻ አካላትን አማክሮ በማሻሻል ማፀደቅ፣ ተደራሽነቱንና አሣታፊነቱን ለማረጋገጥ የሚያግዙት ተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈት፣ የምርጫ ጣቢያዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመመዝገብ ታዛቢዎችን ጨምሮ ለባለድርሻ አካላት በቀላሉ ለመለየት እንዲቻሉ የሚያስችል ሥራ መሥራት፣ ለምርጫና ለቢሮ ሥራ የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ማሟላት እንዲሁን የቦርዱን ሠራተኞች ዐቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ እንዲወስዱ ማስቻል ተጠቃሽ ናቸው። ቦርዱ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የምርጫ ቦርድ ተቋማት ጋርም እንዲሁ የልምድ ልውውጥ ሲያደርግ ቆይቷል።

ባሳለፍነው ሣምንት፤ ቦርዱ ከተለያዩ ሀገራት የምርጫ ቦርድ ተቋማት ጋር ልምድ የመለዋወጡ አካል የሆነውን ጉዞ በናይጄሪያ አድርጎ ተመልሷል። በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ የተመራው ቡድን በጉዞው ላይ የተለያዩ ሥራ ክፍል ባለሞያዎች ያካተተ ሲሆን፤ በአቡጃ በሚገኘው የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን በሆነው Independent National Electoral Commission (INEC) ሲደርስም የINEC ዋና ሰብሳቢ በሆኑት ፕሮፌስር ማህሙድ ያኩቡን ጨምሮ በINEC ከፍተኛ አመራሮችና ባለሞያዎች ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ተስፋዬ በንግግራቸው፤ የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን ከዐየር ማረፊያቸው ጀምሮ ላደረገው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፤ ለዲሞክራሲ ተቋማት አንዳቸው ከሌላኛቸው ልምድ እንዲወስዱ የሚያስችል መሰል የልምድ ልውውጥ ማድረጉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና ምርጫ ቦርድ በናይጄሪያ የሚኖረው ቆይታም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል። ምክትል ሰብሳቢው አክለውም ናይጄሪያና ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ተመሳሳይ የሆነ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን የሚጋሩ እንደመሆናቸው መጠን፤ ይኽ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን አቻቸው የሆኑት ፕሮፌስር ማህሙድ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት ቀዳሚውን ሥፍራ ከሚይዙት ተርታ እንደሚያሠልፋቸው፤ ይኽም የኃይማኖትና የብሔር ብዝኅነት ብሎም ፌደራላዊ የመንግሥት ሥርዓት የሚከተሉ ከመሆኑ ጋር ሲደመር ተመሳሳይ ነገሮችን እንዲጋሩ እንደሚያደርጋቸው አስታውሰው፤ ይኽ የልምድ ልውውጥ የናይጄሪያን የምርጫ ሥርዓት በሰፊው ለማወቅ እንደሚረዳና አንዱ ከሌላው የተሻሉ ነገሮችን የሚወስድበት እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ተናግረዋል።

በልምድ ልውውጡ ወቅት ከሁለቱም የምርጫ ተቋማት የተውጣጡ ባለሞያዎች ልምዶቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን፤ ይኽውም የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ እንዲሁም የድኅረ ምርጫ ተግባራትን የሚሸፍን ነው። የምርጫ የሕግ ማዕቀፍ፣ ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ አካታችነት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ግንኙነት፣ የምርጫ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የሎጂስቲክ ጉዳይ በልምድ ልውውጡ ወቅት ትኩረት ካገኙት ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ከመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት የተካሄደው የልምድ ልውውጥ የመሥክ ላይ ምልከታን ያካተተ ሲሆን፤ ይኽውም በናይጄሪያ በቅርቡ ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ በአቡጃ ከተማ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመራጮች ምዝገባን፣ የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን የልኅቀት ማዕከልን፣ የተለምዷዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቤተ-መጻፍት ቤትን አደረጃጀት መጎብኘት ይጨምራል።

በልምድ ልውውጡ የማጠቃለያ ቀን ንግግራቸው፤ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” እና “የኢትዮጵያ የሲቭል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ” በናይጄሪያ በነበራቸው ቆይታ የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ባጠቃላይ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ላደረጉት የተቀናጀ መስተንግዶና የልምድ ልውውጥ ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና ምክትል ሰብሳቢው ተስፋዬ ያቀረቡ ሲሆን፤ ይኽ የአጋርነቱ መጀመሪያ እንደሚሆንና በቀጣይ በጋራ በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። ምክትል ሰብሳቢው በንግግራቸው መጨረሻ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የሚገኙት የGerman Agency for International Development (GIZ) አባላት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

Share this post