የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበትን መድረክ ማካሄድ ጀመረ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ጊዜ ክርክር የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበትን መድረክ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ማካሄድ ጀመረ። ቦርዱ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳውን አስመልክቶ፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያየ ማግሥት የተጀመረውንና እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የክርክር ልምምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበትን ሥልት እንዲያዳብሩበት፤ ቦርዱ በቀጣይ በሚያወጣው ፕሮግራምም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያላቸውን ፕሮግራምና ፖሊሲ ለመራጩ ሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን አማራጮች በይፋ ከማቅረባቸው በፊት ልምድ የሚያዳብሩበት ጠቃሚ መድረክ እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ቦርዱ ቀደም ሲል ፓርቲዎቹ የምርጫ ጊዜ ክርክር ክኅሎታቸውን ሊያዳብሩ የሚያስችል ሥልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በዚኽኛው መድረክም ፓርቲዎቹ ቀደም ሲል በወሰዱት የክኅሎት ማዳበሪያ ሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በቀረቡት 16 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመከራከር የፓርቲዎቻቸውን ዐቋም የሚያንጸባረቁ ሲሆን፤ በየርዕሰ ጉዳዮቹ ላይም ከሁለት እስከ አራት ፓርቲዎች በመድረክ ላይ ወጥተው መከራከሪያቸውን በማቅረብ የመድረኩ ተሣታፊ በሆኑ ተመልካች ፓርቲዎች ሚሥጥራዊ ድምፅ መስጠት እየተካሄደ አሸናፊው እንዲለይ የሚደረግበት መድረክ ነው።
ቦርዱ በቀደመው ዓመት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ የተሻለ አስተዋፅዖ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተለያዩ የዐቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን መስጠቱ ይታወቃል።