የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 143 የሲቪል ማኅበራት የዕውቅና የምሥክር ወረቀት ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 143 የሲቪል ማኅበራት የዕውቅና የምሥክር ወረቀት ሰጠ። ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደውን መደረክ የመክፈቻ ንግግር የቦርድ አመራር አባሉ ተክሊት ይመስል ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም መራጩ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ እንዲመርጥ መረጃ ግልጽ፣ አሣታፊና ሁሉን ዐቀፍ ሊሆን እንደሚገባ፤ ይኽም ሲሆን በሁሉም ቋንቋ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ባካተተ መልኩ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል። የመራጮች ትምህርት የሚሰጡ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፤ ባለሞያዎቻቸው ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆናቸውንና ትምህርቱ የሚጠይቀው በቂ ዕውቀት እንዳላቸው የማረጋገጥ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። ቦርዱ የማስተማሪያ ማንዋል ማዘጋጀቱን የገለጹት አመራሩ፤ የመራጮች ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና የሥነ-ምግባር መመሪያውም የሥራውን ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ እንዲፈጸም ተግባር ላይ እንደሚውል፤ ምርጫ ቦርዱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ለማኅበራቱ ከተሰጠው የዕውቅና የምሥክር ወረቀት በተጨማሪም ለመራጮች ትምህርት ከሚሰጡ የሲቪል ማኅበራት ጋር የተገናኙ የቦርዱ መመሪያዎችና ተፈጻሚነት ስላላቸው የሕግ ማዕቀፎች፣ ትምህርቱን የሚሰጡ ማኅበራት ሚና፣ ስለሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ አካታችነትን በተመለከተ መሠረታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ በቦርዱ ባለሞያዎች ተሰጥቷል።
ተሣታፊዎቹ ቦርዱ የቅድመ-ምርጫ ተግባራቱን በስኬት በማከናወን ላይ መሆኑን አድንቀው፤ የመራጮች ትምህርት መስጫ ቁሳቁሶች በብሬል ጊዜውን ጠብቀው ስለመዘጋጀታቸው፣ ትምህርት መስጫዎቹ ቦርዱ አሁን ተተርጉመው እንዲቀርቡ ካደረገባቸው በርካታ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንዲተረጎሙ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም የቦርዱ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ የበለጠ ሰፍቶ መሠራት በሚችልበት ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቦርዱ ባለሞያዎች ተሣታፊዎቹ ላነሷቸው አስተያየቶች ማብራሪያ መስጠታቸውን ተከትሎ፤ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግራቸው፤ ቦርዱ ሲቪል ማኅበራትን ማገዝ እና የመራጮች ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ በሚያስችለው ጉዳዮች ላይ በመሥራት ላይ ያለውን ተግባራት ገልጸው፤ ቦርዱ ማኅበራቱን በሁሉም ዐቅሙ ለማገዝ ያለውን ፍላጎት አስረድተዋል። ሜላትወርቅ በንግግራቸው ሲቪል ማኅበራቱ “የምርጫ ማፒንግ” በጋራ በመሥራትና ተደራሽ የሚያደርጓቸውን አካባቢዎች ተናበው በመከፋፈል የበለጠ መሥራት የሚያስችላቸውን ተግባራት እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል። በተያያዘም ተፈናቃዮችን ተደራሽ በሚያደርጉበት ጊዜ በመራጭነት ሳይወሠኑ ራሳቸውን በዕጩነትም ማቅረብ እንዳለባቸው የግንዛቤ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቦርዱ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ሕጋዊ ሰውነት ላላቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማት፤ የማስተማር ፈቃድ እንደሚሰጥ፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይደነግጋል።