Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጠናቀቀው ሣምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ-መንግሥቱ ላይ በተቀመጠውና በቦርዱ ማቋቋሚያ ዐዋጀ ላይ በተደነገገው መሠረት ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል፤ በዚኽም መሠረት ቦርዱ በተጠናቀቀው ሣምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅትም ሁሉም የቦርድ አመራር አባላትና የጽ/ቤት ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ በቦርዱ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ ግምገማና የመማማር ሥራ ክፍል ከፍተኛ ባለሞያ አማካኝነት ቦርዱ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እያደረገ ያለውን ዝግጅን ጨምሮ እስካሁን የሠራቸውንና በመሥራት ላይ ያላቸውን ዋና ዋና ተግባራት በዝርዝር ቀርቧል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቦርዱ ከፍተኛ ባለሞያ አማካኝነት በቀረበዉ ዝርዝር አፈጻጸም መደሰታቸውን ገልጸው፤ ቦርዱ ከዚኽ ቀደም ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ባደረገው ውይይት ላይ የተነሡ ጉዳዮችን ተፈጻሚ ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው ማብራሪያ ቢደረግባቸው ያሏቸውን ነጥቦችም በዝርዝር አንሥተዋል። የአካባቢ ምርጫ ለረዥም ጊዜ ሳይካሄድ መቆየቱን፣ የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ተደራሽነትን ማስፋፋትን በተመለከተ፣ የቦርዱን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አደረጃጀትንና ለምርጫ ሥራ ዝግጁ ማድረግን፣ የሰው ኃይል ማብቃትንና ወደ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት የመሸጋገር ጉዳይ በውይይቱ ወቅት ከተነሡት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ሆነው ይጠቀሳሉ።

ከላይ የተጠቀሱትና ማብራሪያ የተጠየቀባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የአካባቢ ምርጫን አስመልክቶ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ምላሽ፤ የአካባቢ ምርጫ ብዙ የሰው ኃይልና በጀት እንደሚጠይቅ አብራርተው ቦርዱም ይኽን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዕቅድ አውጥቶና ዝርዝር ተግባራትን ለይቶ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት 2017 ዓ.ም. ጨምሮ ለተከበረው ምክር ቤት የበጀት ጥያቄ ማቅረቡን፤ በጀቱ ተፈቅዶ እስከሚለቀቅም በጀት የማይጠይቁ የአካባቢ ምርጫን ለማካሄድ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄውን ከማንሣቱ ጎን ለጎን ቦርዱ ላቀረበው ጥያቄ ተፈጻሚነት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግለት ቦርዱ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ (Lesson Learned Assessment) በገለልተኛ ዓለም ዐቀፍ አማካሪዎች ጭምር እንዲጠና ማድረጉን፤ በጥናቱም ላይ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማጠናከርን፣ የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግን፣ መዋቅራዊ እና የሰው ኃይል አደረጃጀት እና የዐቅም ማሳደግን፣ በስትራቴጂካዊ ዕቅድ መመራትንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥናቱ ትኩረት መሰጠቱን በመጥቀስ፤ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ከማጠናከር አንጻር ቦርዱ ከጥናቱ ግኝት በመነሣት የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ማፅደቁን፣ የሥራ መደቦች፣ የበጀት፣ የሰው ኃይል ምልመላና ምደባ እንዲሁም ቅጥር መመሪያዎችን በማፅደቅም ብቁ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ሠራኞችን በመመልመል ምዳባ እያደረገ መሆኑን፤ በተጨማሪም በቁሳቁስ የማደራጀት ሥራም ጎን ለጎን እየተሠራ መሆኑን በቦርዱ ጽ/ቤት ለተገኙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በስፋት ተብራርቷል። ይህ የማደራጀት ሥራ ሰፊ በመሆኑ አዲስ በሚቋቋሙ ቅ/ጽ/ቤቶች ላይ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱን ተገልጿል።

ከላይ በተጠቀሰው የ(Lesson Learned) ጥናት መነሻነትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኘውን መረጃ መነሻ በማድረግ፤ በምርጫ ወቅት ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የሆኑና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን አንቀጾችን በመለየት ሀገራዊ ተጨባጭነትና ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችን ያገናዘበ ማሻሻያ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ በማድረግና በባለድርሻ አካላት በማስተቸት ጭምር ለተከበረው ምክር ቤት አንዲፀድቅ መቅረቡ ተገልጿል።

ቦርዱ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የዕጩዎችንና የመራጮችን መጉላላትን ለመቀነስ እንዲሁም መረጃን ዘመናዊ ሥርዓትን ጠብቆ ለማደራጀት ያግዘዉ ዘንድ ቦርዱ የዲጂታይዜሽን ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን፤ ከዚኽም ውስጥ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት የሚከናወንበትን ሲስተም አበልጽጎ የፍተሻ ሥራ ማጠናቁን እና ለባለድርሻ አካላት ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። መራጮችም በዕውቀት ላይ የተመሠረት ምርጫ አንዲያደርጉ ከማስቻል አንጻርም፤ ቦርዱ የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ለተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍል፤ በጎ ፈቃደኛ ለሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጭምር በስፋት ሥልጠና በመስጠት ላይ መሆኑ በማብራሪያው ወቅት ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንዴሞ በበኩላቸው ቦርዱ እየሠራ ያለውን ተቋምን የማደራጀትና የማዘመን ሥራ አድንቀው፤ በቦርዱ በአጽንዖት የተጠቀሰውን በቋሚ ኮሚቴው በኩል ሊደረጉ የሚገቡ ተገቢ ድጋፎችን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ አሁን ካለው የተሻለ ኮሚኒኬሽን በመፍጠርና ተቀራርቦ በመሥራት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። ቦርዱ እንደ አዲስ ከተቋቋመ ጀምሮ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ስብሰባ ሲያደርግ ይኽ ለሁለተኛ ጊዜው ነው።

Share this post