የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥነ-ዘዴውን የተመለከተ ዐውደ-ጥናት አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካሪ ድርጅት ቀጥሮ ያሠራው የቦርዱን የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥነ-ዘዴ የገመገመ መነሻ ጥናት መጠናቀቁን ተከትሎ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው ዐዋደ-ጥናት፤ የጥናቱን ሂደትና ግኝት እንዲሁም ጥናቱን ተከትሎ የተሰጠውን ምክረ-ሃሳብ በአማካሪ ድርጅቱ ባለሞያዎች አማካኝነት ዐውደ ጥናቱ ላይ ተሣታፊ ለነበሩት የቦርዱ አመራሮች፣ ለሚመለከታቸው የቦርዱ ሥራ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት አቅርቧል።
የመነሻ ጥናቱ በሁለት ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ማለትም በጋምቤላና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች የተካሄደ መሆኑን የተናገሩት የቦርድ አመራር አባሉ ዶ/ር አበራ ደገፋ፤ የጥናቱን ዋና ዋና ዓላማዎች ሲገልጹም አንደኛ በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በቦርዱ እየተሰጠ የሚገኘው የመራጮች ትምህርት ላይ ያላቸውን ዕውቀትና አመለካከት እንዲሁም ልምምድ መገምገም ነው ያሉ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ዐላማው አሁን ላይ ያለው የመራጮች ትምህርት ተደራሽ እየተደረገበት ያለበትን ሥነ-ዘዴ ውጤታማነትን መፈተሽ ነው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ትምህርቱ እየተሰጠበት ያለበት ሥነ-ዘዴ ከአካታችነት አኳያ ተጋላጭና ትኩረት ላላገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አመቺ መሆኑን መገምገም የጥናት ዓላማው አንዱ አካል መሆኑን ጥናቱን ያስተባበረው የቦርዱ የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ኃላፊው ጨምረው አብራርተዋል።
የአማካሪ ድርጅቱን ባለሞያዎች ማብራሪያ ተከትሎ የዐውደ ጥናቱ ተሣታፊዎች፤ መሰል የምርምር ጥናቶች ቦርዱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ውጤታማነት በመገምገም፤ አበረታች የሆኑትን አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸው ላይ ደግሞ ማስተካከል ለማድረግ ዕድል የሚሰጡ መሆኑን ተናግረው፤ ወደፊትም በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረግ የተቋሙ ባህል ሆኖ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። በተጨማሪም የተደረገው ጥናት በተጠቀሱት የሀገሪቱ አካባቢዎች ብቻ ሳይወሠን ሁሉንም የሀገሪቱ ክልሎች ያሣተፈ ሰፊ ጥናት ተካሂዶ ጥናቱ የተሟላ ሀገራዊ ምሥል እንዲኖረው ማስቻል ተገቢ እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።
በመጨረሻም በዐውደ-ጥናቱ የመዝጊያ ንግግራቸው የቦርድ አመራር አባሉ ዶ/ር አበራ ደገፋ ጥናቱን ያካሄደውን ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ የተባለ አማካሪ ድርጅት አመስግነው፤ የዚኸን መነሻ ጥናት ምክረ-ሃሳቦች በትኩረት በማጤን ቦርዱም ይሁን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቀጣይ በሚኖሩን የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን የተመለከቱ ዕቅዶቻችን ላይ በግብዓትነት ማካተት አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።