Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማሻሻል ላይ ያለው ዐዋጅ ረቂቅን በሲቭል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች አስተቸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ዐዋጅ ቁጥር ቁጥር 1162/2011" ላይ ያደረገውን የዐዋጅ ማሻሻያ በተመለከተ ባሳለፍነው ሣምንት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ለመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች በማቅረብ ማስተቸቱ ይታወቃል። ቦርዱ ይኽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ ዐዋጁ ላይ የሚያደርገውን ውይይት ቀጥሎ በተያዘው ሣምንትም ማለትም ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. የረቂቅ ዐዋጅ ማሻሻያን ለሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶችና ለመገናኛ ብዙኃኑ አከላት ተወካዮች በማቅረብ ከተሣታፊዎቹ ሃሳብ አስተያየት ተቀብሏል።

የቦርድ አመራር አባላት ጭምር የተገኙበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ 6ኛው ሀገረዊ ምርጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ከወሰዳቸው አስተያየቶችና ምርጫውን ተከትሎ በነበሩት የድኅረ-ምርጫ የምክክር መድረኮች ላይ የወሰዳቸውን ግብዓት ለዐዋጁ መሻሻል እንደዋነኛ ገፊ ምክንያት ጠቅሰው፤ ጊዜው የሚጠይቀውን ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችን ከግምት ያስገባና በቴክኖሎጂም የታገዘ አፈጻጸምን ለማረጋገጥ እንዲሁም በጊዜያት ተለዋዋጭነት ውስጥ ለረጅመ ጊዜ ማገልገል በሚያስችል መልኩ ዐዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን ገልጸዋል። የዋና ሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎም የቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ባለሞያዎች ዐዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በዝርዝር ለተሣታፊዎች ያስረዱ ሲሆን፤ በማስከተልም ተሣታፊዎቹ አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል።

የመድረኩ መጠናቀቅን ተከትሎም የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት ዋና ሰብሳቢዋ፤ የቦርዱ ባለሞያዎች ይኽን ማሻሻያ ሲሠሩ በከፍተኛ ትጋትና ኃላፊነት መሆኑን አስታውሰው አመስግነዋል። በተጨማሪም የቴክኒክ ድጋፍ ላደረገው International Foundation for Electoral System (IFES)ምስጋና አቅርበዋል።

ቦርዱ በዐዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ውይይት ሲያደርግ ይኽ ሦስትኛ ዙር ሲሆን፤ በቀጣይም ከቀሪ ባለድርሻ አካላት ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሂደቱ የሚቀጥል ይሆናል።

Share this post