Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ - የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 - የረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ምክረ ሃሳብ ለመሰብሰብ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ከመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ጋር መከረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላለፉት ስድሰት ዓመታት ስራ ላይ ያዋለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ለማሻሻል በሁለት ዙሮች ለሁለት ቀናት በቆየ መርሃ-ግብር ከፓለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ጋር በመወያየት ጠቃሚ ግብዓቶችን መሰብሰብ ቻለ።

አዋጁን ለማሻሻል መሠረታዊ ምክንያቶች ከሆኑት መካከል በ2013 ዓ.ም. እና በ2014 ዓ.ም. የተካሄደውን ስድስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ የተገኙ የአፈፃፀም ተሞክሮዎች፤ ተግዳሮቶችና የግምገማ ውጤቶች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለይተው በተወያዩባቸው ዋና ዋና ስምንት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተነሱ ጭብጦች፣ ቦርዱ በተለያዩ ፓርቲዎች ላይ በወሰነው ውሳኔ መነሻ በተለያዩ ደረጃ ባሉ በፍርድ ቤቶች ሰበር ሰሚ ችሎት ጭምር ደርሰው የተወሰኑ የመጨረሻ ውሳኔዎች እና ሌሎች ሀገሮች የሚጠቀሙባቸው የምርጫ ስራ መርሆችንና የምርጫ ኦፖሬሽንን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ፍላጎቶች ይገኙበታል።

እየተካሄደ ያለው አዋጁን የማሻሻል ሂደት፤ በባለድርሻ አካላት መካከል ግልፀኝነት፣ መተማመን፣ የጋራ መግባባት፣ እና የትብብር መንፈስን ያጎለብታል ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት አስፈላጊነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም መጎልበት፣ የመራጮች የዴሞክራሲና የሲቪክ መብቶቻቸው እና ግዴታዎች ላይ ያላቸው ግንዛቤ ማደግ እና የዓለም አቀፍ የምርጫ አስተዳደር መዘመን ከስድስት ዓመታት በፊት ፀድቆ በተግባር ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ለማሻሻል ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነዋል ብለዋል።

በቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ባለሙያዎች የቀረበው የሕግ ማሻሻያ ረቂቅ ግልፅነት የጎደላቸውን የአዋጁን አንቀፆች በማብራራት፤ አዳዲስ ድንጋጌዎችን በማካተት አላስፈላጊና በአፈፃፀም ላይ ችግር የፈጠሩ አንቀፆችን በመሰረዝ ብሎም የዓለም ዓቀፍ መልካም ተሞክሮዎችን በማካተት ማሻሻያ ተደርጎበት እንደቀረበ ታውቋል።

ወ/ሮ ሜላትወርቅ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ እዚህ ደረጃ ደርሶ ለአውደ ጥናት እንዲበቃ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ረቂቁን በማዘጋጀት እና በማጠናቀር አመርቂ ሥራ የሠሩትን የቦርዱን የሕግ ሥራ ክፍል ባለሙያዎች እና በሰነድ ዝግጅት፣ በጥናት፣ በትርጉም ሥራ፣ በምክር፣ እንዲሁም አውደ ጥናቶችን በማመቻቸት የባለሙያ እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ላለው ለምርጫ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን (IFES) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይ ቀናት በረቂቅ የአዋጁ ማሻሻያዎች ላይ ምክረ ሃሳብ የማሰባሰብ ሥራው ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች፣ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስት ተቋማት አመራሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

Share this post