Skip to main content

ቦርዱ ያዘጋጀውን የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ማንዋልን ለማዳበር የሚረዳ አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ድጋፍ በአማካሪ ተቋም ያስጠናውን በ 2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ሢሠራበት የነበረውን የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ማንዋል የሲቪል ማኅበራት ድርጅት አመራሮች፣ ተወካዮች፣ የቦርዱ የፌደራል እና የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊዎች እና የስነ-ዜጋና አካታችነት ባለሙያዎች በተገኙበት በመገምገም ሰነዱን የሚያዳብሩ ጠቃሚ ግብዓቶችን ሰበሰበ።

በቦርዱ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት በተዘጋጀው አውደ ጥናት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ማንዋሉ መራጮች ከተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡላቸውን የፓለቲካ ፕሮግራም አማራጮች ተገንዝበው፤ በእውቀት ላይ ተመስርተው ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ ከማስቻሉም ባሻገር፤ የመራጮች በምርጫ ቀን ወጥቶ ለመምረጥ ያላቸውን ተነሳሽነት ያሳድጋል ብለዋል።

የዚህ አውደ ጥናት ዋንኛ ዓላማ ማንዋሉሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት፤ ከባለድርሻ አካላት የመጨረሻ ግብዓቶችን አሰባስበን ግልፅ፣ በቀላሉ ሊተገበር የሚችል እና ውጤታማ ሰነድ ለማሰናዳት ያለመ ነው ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ይህ ማንዋል እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ ትጋት ላሳዩት የቦርዱ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች እና ለተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ማንዋሉ በአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በዋነኛነት ከይዘት አንፃር ትክክለኛ መረጃና እውነታን ከመያዝ፣ ከተገቢነት፣ ከወቅታዊነት፣ ሰነዱ እንዲዘጋጅ ምክንያት ከሆኑ ዓላማዎች፣ ስነዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ከሚሰጥበት ስልት ውጤታማነት፣ በአሠልጣኝና በሠልጣኞች መካከል ከሚኖረው የመማርና የማስተማር መስተጋብር፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከማካተት አኳያ፣ ንድፈ ሃሳብን ከተግባራዊ ሥልጠና ጋር አጣጥሞ ትምህርቱን ከመስጠት እና ሥልጠናው ውጤታማ ለመሆኑና ላለመሆኑ ከመገምገሚያ ዘዴዎች አንፃር በዝርዝር ተፈትሾ ጠቃሚ ግብዓቶች እንደተሰበሰቡ ታውቋል።

በአውደ ጥናቱ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል አበራ ደገፋ (ዶ/ር) ማንዋሉ በዋነኛነት ትኩረት ያደረገው መራጮች ላይ በመሆኑ፤ እንደ መራጮቹ ማንነት እና ነባራዊ ሁኔታ ማንዋሉ ተቃኝቶ መተግበር ግድ ይላል ብለዋል።

ማንዋሉ ከምርጫ ዑደቶች (ከቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እንዱሁም ከድኅረ ምርጫ) ትኩረት ተሰጥቷቸው በስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ማዕቀፍ ለዜጎችና ለመራጮች ሊሰጡ የሚገባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑ ታውቋል

Share this post