Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፆታዊ ትንኮሳን የተመለከተ ፓሊሲ እና የማስተግበሪያ ሥነ-ሥርዓት (procedure) ለሠራተኞቹ አስተዋወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቴክኒክ ቡድን አዋቅሮ አንድ ዓመት በወሰደ ጊዜ ያስጠናውን የፆታዊ ትንኮሳ ፓሊሲ እና የማስተግበሪያ ሥነ-ሥርዓት (procedure) በፌደራል እና በክልል ለሚሰሩ የቦርዱ ጏላፊዎችና ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት አስተዋወቀ።

በአውደ ጥናቱ በዋንኛነት የፆታዊ ትንኮሳ ፓሊሲ እና የማስተግበሪያ ሥነ-ሥርዓት አስፈላጊነት፣ የፆታዊ ትንኮሳ ባህሪያት እና መገለጫዎች፣ የፆታዊ ትንኮሳ ክስ የሚቀርብበት ሥነ-ሥርዓት፣ የፓሊሲው የተፈፃሚነት ወሰን እና ፆታዊ ትንኮሳ በሚያስከትለው ችግሮች ላይ ገለፃ ተሰጥቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙያዊ ሥነ-ምግባራቸውን ጠብቀው የሚሰሩ ባለሙያዎች እና ጏላፊዎች ያሉበት ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋም ነው ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ጏይሉ ይህ የፆታዊ ትንኮሳ ፓሊሲ እንዲወጣ የወሰንበት ዋንኛ ምክንያት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሊፈጠሩ የሚችሉ የፆታዊ ትንኮሳዎችን ለመከላከል ብሎም ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢን በአስተማማኝ መደላድል ላይ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

ፓሊሲው በሚተገበርበት የተፈፃሚነት ወሰን ከፆታ ትንኮሳ ጋር በተያያዘ ለሚፈፀሙ ጥሰቶች ቦርዱ የሚከተለው አቅጣጫ ጠንካራና ምንም የማይታገሱት (Zero tolerance) መርህ ነው ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ፓሊሲውን በውስጥ አቅም ያለምንም የውጪ አማካሪ አጥንተው እዚህ ደረጃ ያደረሱትን የቴክኒክ ቡድን አባላት አመስግነዋል።

ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ እና ለህግ ጥበቃና ተገዢነት መዳበር ከፍተኛ ሚና የሚኖረው የፆታዊ ትንኮሳ ፓሊሲ እና የማስተግበሪያ ሥነ-ሥርዓት በየደረጃው ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Share this post