Skip to main content

የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም /United Nation Development Program-UNDP/ ጋር በ (SEEDS2) ፕሮጀክት ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ ዙሪያ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮገራም /United Nations Development Program-UNDP /ለምርጫ ቦርድ በሚሰጠው የ(SEEDS2) ፕሮጀክት ድጋፍ እኤአ በ2025 ዓመት ሊሠሩ የታሰቡ ሥራዎችን ለማቀድ በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ከቦርዱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡ የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማም የቦርዱ ሥራ ክፍሎች ከUNDP (SEEDS2)ፕሮጀክት የሚያገኟቸውን ድጋፎች ተከትሎ የሚሠሯቸውን ሥራዎች በተገቢው መንገድ እንዲያቅዱ ማስቻል እና የምርጫ ቦርድን የሥራ ዕቅድና የዕቅድ አፈፃፃም ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ ያለመ ነበር፡፡

ለሶስት ቀናት በቆየው አውደ ጥናት ውጤት ተኮር ሥራ አመራርን /Result Based Management/ በተመለከተ በፅንሰ ሃሳቡና በአተገባበሩ ዙሪያ በ UNDP ባለሙያዎች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን ይኽውም ዕቅዶች ሲታቀዱ ሊለኩ የሚችሉ፤ በአተገባበር ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችን እየነቀሱ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ እና አደጋን ቀድመው ማየት የሚችሉ / Risk Informed / ሆነው መታቀድ እንዳለባቸው ውይይት ተደርጓል፡፡

ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ /Annual work plan / ሲዘጋጅ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነገሮችን በተመለከተ በተደረገው ውይይትም የቦርዱ ስትራቴጂክ ዕቅድ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተለዋዋጭ ሁነቶች/Emerging Situations/ከግምት መግባት እንዳለባቸው እና የቦርዱ የሥራ ክፍሎች ዕቅዶቻቸውን ሲያቅዱ የባለድርሻ አካላትን ባማከለ መልኩ ማቀዳቸው ዕቅዶቻቸው በተፈለገው መጠን ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም ባሻገር ተደራራቢ ጥረቶችን /duplication of efforts// ወይም አላስፈላጊ የሆኑ የሰው ኃይልና እና የኃብት ብክነቶችን ለመከላከላል እንደሚያስችል ተወስቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ውጤት ተኮር የዕቅድ ዘገባ /Result Based Reporting/፤ውጤት ተኮር የዕቅድ ክትትል/ Result Based Monitoring/ እና ውጤት ተኮር የዕቅድ ግምገማ /Result Based Evaluation/ በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራሞችን ዘገባ፤ ክትትልና እና ግምገማ ቴምፕሌትን መነሻ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይትና የተግባር ልምምድ ተደርጓል ፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ በUNDP SEEDS2 ፕሮጀክት ባለሙያዎች አማካይነት እኤአ በ2025 ለምርጫ ቦርድ በሚሰጧቸው የድጋፍ ዘርፎች እና በጀት ዙሪያ ዕቅዶቻቸውን አቅርበው በቀረበው የሥራ እቅድ እና የበጀት አፈፃፀሞች እና በተገመቱ ተግዳሮቶች ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የቀረቡት ዕቅዶች ከቦርዱ ፍላጎት እና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት አንፃር ምን ያህል ሊጣጣሙ እንደሚችሉ ተፈትሸዋል፡፡

በስተመጨረሻም በአውደ ጥናቱ ላይ የምርጫ ቦርድ ሥራ ክፍሎች በየፕሮግራሞቻቸው በ UNDP SEEDS 2 ድጋፍ ሊሠሩ ያቀዷቸውን ተግባራት በጋራ አቅደው ዕቅዶቻቸውን በማቅረብ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Share this post