የኢትዮጽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሥራ ላይ ያለው ሕግን ማሻሻል የተመለከተ ዐውደ-ጥናት አካሄደ
የኢትዮጽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በሥራ ላይ ያለው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011” የተመለከተ የሕግ ማሻሻያ ዐውደ ጥናት አካሄደ።
አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት፣ የየሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች እንዲሁም የቦርዱ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች የተገኙበትን ዐውደ-ጥናት በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ስድስተኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫን ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄዱ የድኅረ-ምርጫ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ግምገማ መድረክ ላይ የተነሡትን የሕግ ማሻሻያ የሚፈልጉ ዐዋጁ ላይ ያሉ ድንጋጌዎች ፤ ከሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀደም ብሎ በመለየት፤ ዓለም ዐቀፍ መመዘኛዎችን ባማከለና የተሻለ አፈጻጸምና ግልጸኝነትን ለማጎልበት እንዲረዳ ተደርጎ ማሻሻያ እንደተደረገበት ተናግረዋል።
ዋና ሰብሳቢዋ አክለውም፤ ማሻሻያ አንዲደረግባቸው የቀረቡት የአዋጁ አንቀፆች ማሻሻያዎች ከመፅደቃቸው በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን ፤ የቦርዱ አመራሮችና የተለያዩ የስራ ክፍል ሀላፊዎች በቅድሚያ እንዲወያዩና ግባት አንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህው አውደ ጥናት መዘጋጀቱን ገልፀው የቦርዱ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በአውደጥናቱ ላይ በትጋት አንዲካፈሉ አሳስበዋል።
በቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ባለሙያዎች አማካኝነት የቀረበው የሕግ ማሻሻያ ረቂቅላይ ገልፅነት የጎደላቸውን ሀሳቦች በማብራራት አዳዲስ ደንጋጌዎችን በማካተት አላስፈላጊና በአፈፃፀም ላይ ችግር የፈጠሩ አንቀፆችን በመሰረዝ እና በተጨማሪ የዓለምዓቀፍ መልካም ተሞክሮዎችን በማካተት ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበ ሲሆን፤ ዝርዝሩም በቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ባለሞያዎች አማካኝነት ለመድረኩ ተሣታፊዎች ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
በተጨማሪም በበምርጫ ጊዜ በሚጠይቃቸው ተለዋዋጭ ወቅታዊ ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ በመክተት የቦርዱን ገለልተኛነትና መሰረታዊ የሆኑ መብቶችን የማይጎዱ ተግባራት ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ እንዲወሠኑ የሚፈቅድ ይሆናል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው ዐዋጅ ከወጣ ስድስት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ ቦርዱ አንድ ሀገራዊ ምርጫና ሦስት ሕዝበ ውሣኔዎችን አስፈጽሟል።