Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) SEEDS ፕሮጀክት ያስገኘውን እና እያስገኘ ያለውን ፋይዳና ጠቀሜታ አስመልክቶ ውይይት አደረገ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) SEEDS ፕሮጀክት ያስገኘውን እና እያስገኘ ያለውን ፋይዳና ጠቀሜታ አስመልክቶ ከ UNDP SEEDS ፕሮጀክት አስተባባሪ አካላት፣ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ከልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ውይይት አደረገ።

የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ቀደም ሲል ለነበረው ድጋፍ እውቅና ለመስጠት እና ለነባር የ SEEDS ፕሮጀክት እና አዳዲስ አጋሮች ምርጫ ቦርድን እንዲደግፉ ለማበረታታት እና ስለ ምርጫ ቦርድ እድገት እና የትኩረት አቅጣጫዎች ለአጋር ድርጅቶች ለማስረዳት ያለመ ነበር።

ከ SEEDS ፕሮጀክቶች ዋነኛ ዓላማዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠንካራ ተቋማዊ ቁመና ያለው፣ የአሠራር ሥርዓቱ ግልጽ የሆነ እና በመራጮች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ተቋም እንዲሆን መሥራት ነው፡፡

ከአጋር የልማት ተቋማት ጋር በተደረገው የውይይት መድረክ የመክፈቻ መልእክታቸው SEEDS ፕሮጀክት የተጠነሰሰው የቦርዱን አቅም በማጠናከር ውስብስብ በሆነው የምርጫ ከባቢ ምርጫዎችን በነፃነት፣ ገለልተኝነት እና ብቃት ለማስፈፀም በማለም ነው ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በ SEEDS አንድ እና SEEDS ሁለት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በምርጫ ቦርዱ ላይ የሕዝቡ አመኔታ እና መተማመን ይበልጥ እንዲጎለብት እና ቦርዱ በነፃነት ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ጠብቆ እንዲሠራ ላደረገው እገዛ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

የ SEEDS ፕሮጀክት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተጨማሪም የሌሎች አጋር የልማት ድርጅቶች ድጋፍ በተለይ በያዝነው ዓመት በሁለት ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ቦርዱ ለሚያካሂደው አካባቢያው ምርጫ እና በ2018 ዓ.ም ለምናደርገው 7ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ሊደርስልን ይገባል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሪዚደንት ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ SEEDS ፕሮግራም በተደረገለት ድጋፍ ቦርዱ ላይ አመርቂ የሚባል ለውጥ ማምጣት በመቻሉ ሌሎችም የልማት አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በ SEEDS አንድ ፕሮጀክት ከተሰጡ ድጋፎች መካከል የአቅም ግንባታ ሥራዎች (ሥልጠናዎች፣ የባለሙያዎች ቅጥር)፣ ከግዥ አኳያ የምርጫ ቁሳቁሶች፣ የቦርዱን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ተግባርት መደገፍ፤ የመራጩን ግንዛቤ ለማሳደግ የተደረጉ የመራጮች ትምህርት እና የሚዲያ ቅስቀሳ ሥራዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ድጋፉ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሎሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት በአግባቡ ተካተው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና በሀገረቷ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ልማት እንዲረጋገጥ ብሎም የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን ለማጎልበት የተደረገ ዕገዛ መሆኑ ታውቋል::

እ.ኤ.አ ከ2023 ጀምሮ እስከ 2027 በሚቆየው SEEDS ሁለት ፕሮጀክት ደግሞ በዋነኛነት በ SEEDS አንድ የተጀመረውን የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት እና ሂደትን የማጠናከር ሥራ፣ አካታችነት፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ የመሥራቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑ ታውቋል።

በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ ላይ ከውይይቱ ተሳታፊ አካላት ለተነሱ ጥያዌዎች የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ምላሽ ከሰጡ በኃላ ተጠናቋል።

.

Share this post